
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የፊንላንድ የውጭ ንግድ እና ልማት ሚኒስትር ቪሌ ታቪዮ በዚህ ሳምንት በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉ ሲኾን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በንግድ እና በኢንቨስትመንት መስክ ያላትን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሠራ ሚኒስትሩ ቪሌ ታቪዮ ገለጸዋል።
ሚኒስትሩ ቪሌ ታቪዮ በተለይ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላት ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁ የፊላንድ የልማት ትብብር አጋር ሀገር መኾኗን ጠቅሰው በውኃ፣ በግብር እና በትምህርት ዘርፎች በትብብር እየሠራች መኾኑን አንስተዋል።
ፊንላንድ በኢትዮጵያ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካው መስክ የሚካሄዱ የሪፎርም ሥራዎችን ለማገዝ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2021 እስከ 2024 የሚቆይ የ75 ሚሊዮን ዩሮ ፕሮጀክት ቀርጻ እየተገበረች ነው። ፊንላንድ በውኃ ዘርፍ በምታደርገው ድጋፍ በኢትዮጵያ የንጹህ ውኃ አገልግሎት ተደራሽነትን ማገዝ መቻሉን ገልጸው በተመሳሳይ በግብርና እና በትምህርት የትብብር መስኮችም አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ነው የገለጹት። በዚህ የድጋፍ ማዕቀፍ በኢትዮጵያ የተሠሩት ሥራዎች የእስካሁኑ አፈጻጸማቸው ስኬታማ መኾኑን እና ትብብሩን በቀጣይም ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሠራ ገልጸዋል። በተለይም ከኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በቅድመ ጥንቃቄ የትንበያ መረጃ ሥራዎች ላይ በጋራ ለመሥራት እቅድ መኖሩን ጠቁመዋል። በዘመናዊ ግብርና ፊንላንድ የተሻለ አፈጻጸም ያላት ሀገር መኾኗን ጠቅሰው በዚህ ዘርፍ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
በሌላ በኩል ፈንላንድ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋን ለማጠናከር እንደምትሻ ገልጸው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ትሠራለች ነው ያሉት። ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የፊንላንድ ብቻ ሳይኾን የአውሮፓ ኅብረት የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትኾን ሀገራቸው ፍላጎት እንዳላት ጠቅሰው ለዚህም ይሠራል ነው ያሉት። በተለይም የኢትዮጵያን የማኑፋክቸሪንግ መስክ የበለጠ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲያገኝ ለማድረግ በትምህርት ዘርፍ ፊንላንድ ድጋፏን እንደምታጠናክር ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለማቋቋም የምታከናውነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ሊበረታታ የሚገባው ሥራ መኾኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲኾን ፊንላንድ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል። ሚኒስትሩ ቪሌ ታቪዮ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ በትምህርት ዘርፍ ለመምህራን አቅም ግንባታ የሚውል የ5 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ሥምምነት አድርገዋል።
ኢትዮጵያ እና ፊንላንድ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር በ1959 መኾኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!