“የሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ከግጭት አዙሪት እንዲወጣ እና ሰላማዊ አማራጮች እንዲዘወተሩ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል” ሰላማዊት ካሳ

39

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ለብዙኅን መገናኛ ተቋማት መግለጫውን የሰጡት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ድኤታ ሰላማዊት ካሳ “የመንግሥት የሰላም ፈላጊነት ጽኑ አቋም ትናንትም የነበረ፤ ዛሬም ያለ እና ነገም በተግባር ታጅቦ የሚቀጥል ይኾናል” ብለዋል፡፡

መንግሥት ለሰላም ያለውን ጽኑ ፍላጎት እና የማይናወጥ ወጥ አቋም ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በተደጋጋሚ አሳይቷል ያሉት ሚኒስትር ድኤታዋ ለስኬቱም የተለያዩ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል ነው ያሉት፡፡
“የሀገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ከግጭት አዙሪት እንዲወጣ እና ሰላማዊ አማራጮች እንዲዘወተሩ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል” ያሉት ሚኒስትር ድኤታዋ ሰላማዊት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋም፣ የሽግግር ፍትሕ ሂደት እንዲሳካ ማገዝ እና ሰላማዊ የትግል አማራጮችን አሠራር መዘርጋት ማሳያዎች አድርገው አቅርበዋቸዋል፡፡

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ገለልተኛ ኾኖ እንዲቋቋም ከማድረግ ባሻገር ሂደቱ እንዲሳካ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግም አንስተዋል፡፡ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከዓለም አቀፍ ጥልቅ ጥናት እና ምርምር የመነጨ እና ሀገር በቀል እሴቶችን ያንሰላሰለ ኾኖ እንዲቀጥል በኀላፊነት ስሜት እየተሠራ እንደኾነም አንስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ተሻግሮ ወደ አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት መግባቱም በኢትዮጵያውያን ዘንድ በትኩረት፣ በተስፋ እና በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡ ሂደቱን መንግሥት በቁርጠኝነት ይደግፋል ያሉት ሚኒስትር ድኤታዋ ሁሉም የማኀበረሰብ ክፍል ድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ሌላው ሚኒስትር ድኤታዋ ያነሱት ነጥብ ነፍጥ አንግበው መንግሥትን በኃይል ለመጣል የሚሞክሩ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ አማራጮች መመለስ ቢፈልጉ የሚስተናገዱበት ሕጋዊ አሠራር መዘርጋቱን ነው፡፡ ግጭት እና ጦርነት ደጋግሞ በሚፈትናት ኢትዮጵያ ውስጥ ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ሰላማዊ የትግል አማራጮችን ለመጠቀም ቢፈልጉ የሚስተናገዱበት የሕግ ማዕቀፍ አልነበረም ያሉት ሚኒስትር ድኤታዋ ሰላማዊት ካሳ ከሰሞኑ የአዋጅ ማሻሻያ መድረጉን አንስተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ድኤታዋ ገለጻ የሀገሪቱ የምርጫ ሕግ ከሕጋዊ እና ሰላማዊ ማዕቀፍ ውጪ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች ወደ ሰላማዊ አማራጮች ለመመለስ ቢፈልጉ ሕጋዊ የፖለቲካ እውቅና ሰጥቶ መመለስ የሚያስችል አሠራር አልነበረም፡፡ ከሰሞኑ የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ይህንን ክፍተት የሚሞላ ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ድኤታዋ በመግለጫቸው የመንግሥት የሰላም ፈላጊነት እና አቋም ትናንትም የነበረ ነው፤ ዛሬም ያለ ነው፤ ወደ ፊትም በተግባር ታጅቦ የሚቀጥል ይኾናል ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተከሰተውን የኮሌራ በሽታ ለመቆጣጠር እየሠራ መኾኑን የሰሜን ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ ገለጸ።
Next article“እንኳን ለ2016 የዒድ አል አድሃ በዓል በሰላም አደረሳችሁ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)