
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ጎጃም ዞን ጤና መምሪያ በዞኑ ስለተከሰተው የኮሌራ በሽታ መግለጫ ሰጥቷል። የመምሪያው ኀላፊ ደሳለኝ ዳምጤ በዞኑ የኮሌራ ክስተትን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም አንዳሳ የጸበል ቦታ ላይ የኮሌራ በሽታ መገኘቱን ተናግረዋል።
ከዚያ ወዲህ በተደረገ ክትትልም ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ቀን ድረስ በባሕር ዳር ዙሪያ ወረዳ አንዳሳ የጸበል ቦታ ላይ 113 እና ይልማና ዴንሳ ወረዳ ጤና ተቋም ውስጥ ደግሞ 2 ሰዎች በኮሌራ በሽታ ተይዘው መገኘታቸውን ገልጸዋል።
በሽታው መከሰቱ ከታወቀ ጀምሮ ዞኑ በትኩረት እየሠራ መኾኑን የጠቀሱት መምሪያ ኀላፊው የመከላከል እና የህክምና ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በሽተኞች እየታከሙ ሲኾን 93 መዳናቸውን እና የሞተ ታማሚ አለመኖሩን ገልጸዋል።
ኮሌራ በሽታ በአጣዳፊ ተቅማት እና ትውከት የሚያስከትል፣ የሰውነት ውስጥ ፈሳሽ እና ንጥረ ነገርን በመጨረስ ከፍተኛ የሰውነት ድክመት የሚፈጥር እና በፍጥነት ካልታከመ ለሞት የሚዳርግ ውኃ ወለድ እና ተላላፊ በሽታ እንደኾነ ነው ኀላፊው የገለጹት።
በሽታው ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያጠቃ ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ በአንድ ቦታ ተከሰተ ማለት ወረርሽኝ ተከሰተ ማለት መኾኑንም ገልጸዋል። በዞኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በሽታው የተገኘበት ሰውም ከባቲ የመጣ ነው፤ ስለኾነም በሌሎች አካባቢዎችም የመከሰት እና የመተላለፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የኮሌራ በሽታ በፍጥነት ከታከመ የመግደል ምጣኔው ከአንድ በመቶ በታች ሲኾን ህክምና ካላገኘ ግን እስከ ሃምሳ በመቶ የመግደል እድል እንዳለው በመግለጫው ተመላክቷል።
የኮሌራ በሽታ መተላለፊያ፦
👉 በባክቴሪያው የተበከለ ምግብ እና ውኃ በመጠቀም፣
👉 በኮሌራ የሞተን ሰው ነክቶ በደንብ አለመታጠብ፣
👉 በየቦታው መጸዳዳት፣
👉 የተበከለ ውኃ መጠቀም መኾናቸው ተመላክቷል።
የኮሌራ ምልክቶች፦
👉 ፋታ የማይሰጥ ተቅማጥና ትውከት፣
👉 የአፍ መድረቅ፣
👉 የአይን መጎድጎድ እና መቅላት
👉 የቆዳ መሸብሸብ እና የድካም ስሜት መኾናቸው በመግለጫው ተመላክቷል። እነዚህ ምልክቶች ሲታዩም በፍጥነት የትኛውም የጤና ተቋም ላይ ህክምና ማግኘት እንደሚቻል ተገልጿል።
በሽታውን ለመከላከልም፦
👉 የግል እና የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ፣
👉 መከላከያ ክትባቱን መውሰድ፣
👉 ሜዳ ላይ ከመጸዳዳት ተቆጥቦ መጸዳጃ ቤት መጠቀም፣
👉 ውኃን አፍልቶ መጠቀም፣
👉 የታመሙ ሰዎችን በፍጥነት ወደ ህክምና መውሰድ እንደሚገባ ኀላፊው አሳስበዋል።
በዞኑ በሽታውን ለመቆጣጠር በመከላከል እና ለማከም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል። የዞን ኮሚቴ ተቋቁሞ ክትትል እየተደረገበት እና እየተመራ መኾኑንም አክለዋል። አንዳሳ ጤና ጣቢያ ላይ ሰባት የማከሚያ ጣቢያ ተቋቁሞ በሽተኞች እየታከሙ መኾኑን እና ስርጭቱም መገታቱን አስታውቀዋል። ሰዎች ለጸበል በሚሰባሰቡበት ጊዜ ለበሽታው እንዳይጋለጡ መደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በውይይት መግባባት ላይ በመደረሱም የበሽታውን ስርጭት መግታት አስችሎናል ብለዋል።
ኮሌራን ለመከላከል የኅብረተሰቡ እና የአጋር አካላትን ጠንካራ ትብብር እንደሚጠይቅ የጠቀሱት ኀላፊው በሽታው በሰሜን ጎጃም ብቻ እንደተከሰተ ታስቦ ዝም መባል እንደሌለበት አሳስበዋል። ምልክቱ እና በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ከተለያዩ ዞኖች የመጡ መኾናቸውንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በሽታው ሊጨምር እንደሚችል ማሳያዎች አሉ፤ ስለዚህ ሁሉም አካል መቀናጀት ይገባዋል ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ። መተባበር፣ መቀናጀት እና መግባባትን የሥራው መርህ አድርገን እንሠራለን፤ ለዚህም ጤና ቢሮ እና ሌሎች አጋር አካላት እየተባበሩን ነው ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!