
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒሰትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ባለፉት 10 ወራት በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ኢትዮጵያ ባለ አምስት ግዙፍ የኢኮኖሚ ባለቤት ስለመኾኗ አስረድተዋል፡፡
ይህንንም ሲያስረዱ ኢትዮጵያ ባለ ብዙ ግዙፍ ኢኮኖሚ ከገነቡ ሀገሮች ተርታ መሰለፏን ገልጸው በዚህም ባለፉት ወራት 7 ነጥብ 9 በመቶ የምጣኔ ሃብት እድገት መመዝገቡን ነው የገለጹት፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገበው የማክሮ ኢኮኖሚ 3 ነጥብ 9 በመቶ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህም የሚያሳየው ኢትዮጵያ የተሻለ የማክሮ ኢኮኖሚ መገንባቷን ነው ብለዋል፡፡ ይህን እድገትም ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ያረጋገጠው እውነታ ስለመኾኑም ነው ያብራሩት፡፡
ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ እንደማሳያ ካነሱት ጉዳይ አንዱ የግብርና እድገቱን ሲኾን በዚህም በሰብል ምርት 513 ሚሊዮን ኩንታል ባለፉት 10 ወራት ለማምረት ታቅዶ 506 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ስለመገኘቱ ነው የተናገሩት፡፡ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት 393 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቶ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ሌላው የእድገቱ ማሳያ የሆልቲ ካልቸር ምርት ሲኾን በዚህም 122 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ 340 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ነው የገለጹት፡፡ ከመሥኖ ሥንዴ ሥራ አኳያ አምና 47 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቶ የነበረ ሲኾን በዚህ ዓመት 106 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ስለመገኘቱ አስገንዝበዋል፡፡ ይህም በምግብ ራስን ለመቻል ታሳቢ ተደርጎ የተሠራው ሥራ ውጤት ለማምጣቱ ማሳያ እንደኾነም ነው የተናገሩት፡፡
በሩዝ ልማትም በኩል አምና 9 ሚሊዮን ኩንታል የተመረተ ሲኾን በዚህ ዓመት 37 ሚሊዮን ኩንታል ስለመመረቱ ነው ያብራሩት፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት በግብርና በኩል ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ተብለው በካቢኔም በየደረጃው ባለው አደረጃጀትም የተገለጸውን ጉዳይ ሲያብራሩ እንዳሉት የሆልቲ ካልቸር ሥራ ትኩረት ተሠጥቶ እንዲሠራ አቅጣጫ ስለመቀመጡ ነው፡፡
ሌላው ጉዳይ በመኽር ላይ ያለው የግብርና ሥራ በግብዓትም በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደተሠራው ሁሉ በበልግ ጊዜ ላለው የግብርና ሥራም ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ መገምገሙን ነው ያስታወሱት፡፡ ከተረጅነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ሕዝብን በስፋት ማሳተፍ አስፈላጊ እንደኾነ ታምኖ አቅጣጫ ስለመቀመጡም አስገንዝበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!