
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉደዮች ከፍተኛ ምክር ቤት እንኳን ለ1445ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብሏል። የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉደዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዚዳንቱ በመልዕክታቸውም “የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓል ለፈጣሪያችን አሏህ ፍጹም ፍቅር እና ፍጹም ታዛዥነትን የምንማርበት፣ ስንተገብረውም የምንድንበት እና አስደናቂ ታሪክ የምናወሳበት የደስታ ቀናችን ነው” ብለዋል። የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓል ማካፈልን፣ አንዱ ለአንዱ መድረስን የምንተገብርበት እና ፍጹም ሰብዓዊ የኾኑ ተግባራት የሚከወኑበት የደስታ እና የአብሮነት ማሳያ በዓል ነው ብለዋል።
የዘንድሮው ዒድ ከየትኛውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ ሰዎች ሊረዳዱ እና ሊተጋገዙ የሚገባቸው ወቅት ነው ያሉት ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ “ይህንን በዓል ስስናከብር በየአካባቢያችን በከባድ ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን በማሰብ፣ በማገዝ እና የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይገባል” ብለዋል። “በዓሉን ስናከብር ያለንን በማጋራት እና የእኛን ደስታ በማካፈል ደስታችን ሙሉ ማድረግ ይኖርብናል” ነው ያሉት።
የምክር ቤቱ የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኀላፊ ኡስታዝ ሀሰን አሊ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ስታዲየም እና አካባቢው በሚደረገው የዒድ ሰላት ላይ ለመካፈል የሚመጣው የከተማወው ሙስሊም ማኅበረሰብ የሚገለገልባቸውን ቦታዎች እና ቁሳቁሶች ንጽህናቸውን እና ደህንነታቸውን መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉ ፍጹም ሰላማዊ ኾኖ እንዲከበር ኀላፊነቱን እንዲወጣ እና የዒዱን ሥነ ስርዓት ለማገዝ ለሚሰማሩ የፀጥታ አካላት የተለመደ ቀና ትብብር ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!