
ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የግብርና ቢሮ በምዕራብ አማራ የሚገኙ የግብርና መምሪያ ኀላፊዎች እና የባለሙያዎች የቴክኒክ ቡድን የ2016/17 የክረምት የሠብል ልማት ሥራዎች ላይ ተወያይቷል፡፡ በመድረኩም የግብርና ቢሮ መሪዎች፣ የምዕራብ አማራ ግብርና መምሪያ ኀላፊዎች፣ ዳይሬክቶሬቶች እና ስምሪት የተሰጣቸው የቴክኒክ ቡድን ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነው፡፡
በመድረኩ የተገኙት ምክትል ቢሮ ኀላፊው አጀበ ስንሻው የባለሙያዎች የቴክኒክ ቡድን ዓላማው በዚህ ወቅት በችግር ውስጥም ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ክፍተቶችን ለመሙላት ታሳቢ ያደረገ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ ቀጣይ ለሚከናወኑ የሠብል ልማት ሥራዎች በግብዓትነት እንዲያገለግሉ የታሰበ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ ትኩረት የሚደረግባቸው የክረምት የሠብል ልማት ሥራዎች ውስጥ የእርሻ ድግግሞሽ፣ የዘር አቅርቦት እና ስርጭት፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ሥራ እንዲሁም የክላስተር ሥራዎችን በልዩ ትኩረት መሥራት እንደሚገባ አቶ አጀበ ተናግረዋል፡፡
የግብዓት አቅርቦት ሥራ በተገቢው ካልተሠራ የሠብል ልማት ሥራ ሙሉ አይኾንም፡፡ በተለይም ምርጥ ዘር በተገቢው ጊዜ መድረሱን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ የሚፈጠር የዘር ስርጭት እና አቅርቦት ክፍተት ተፅዕኖው ከፍ ያለ እንደሚኾንም ተገልጿል፡፡
የክላስተር ሥራን በተጠናከረ መልኩ መሥራት እንደሚያስፈልግ እና ጥቅሙም ላቅ ያለ ስለመኾኑ ነው የተነገረው፡፡
ለክትትል እና ቁጥጥር፣ ለገበያ ትስስር እና መሰል ጥቅሞች ሲባል የዘር ብዜት ሥራን መሠረታዊ ለውጥ በሚያመጣ መንገድ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።
ችግር አለ በማለት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ስለማይቻል ከነችግሩም ቢኾን መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለአረንጓዴ አሻራ ሥራ በተጨባጭ የችግኝ የማጓጓዝ ሥራ እና የጉድጓድ ቁፋሮ የት ደረጃ እንዳለ ማወቅ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
የሌማት ትሩፋት ሥራ በሀገር ደረጃ ልዩ ትኩረት የተሠጠው መኾኑን በመግለጽ በትኩረት መሠራት አለበት፤ ጥቅሙም ቢኾን ከሠብል ልማት ቀጥሎ ተስፋ የተጣለበት መኾኑን በመረዳት መሥራት እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡ በመድረኩ የግብርና መምሪያ ኀላፊዎች እና የባለሙያዎች የቴክኒክ ቡድን አባላት በዞን እና ወረዳ የተመለከቷቸውን በተሠጣቸው ቸክ ሊስት መሠረት በጥንካሬ እና በድክመት በመለየት አቅርበዋል፡፡ የግብርና ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው በቀረበው መድረክም የማሳ መረጣ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የእንስሳት ሃብት ልማት፣ የዘር ብዜት እና የግብዓት አቅርቦትን በተመለከተ በዝርዝር ቀርቧል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!