“የአየር ትራንስፖርትንና ቱሪዝምን ይበልጥ ለማስተሳሰር እየሠራን ነው”አቶ መስፍን ጣሰው

16

ባሕር ዳር: ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የስካይ ላይት ሆቴሎችን በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በማስፋት የአየር ትራንስፖርትንና ቱሪዝምን ይበልጥ ለማስተሳሰር እየተሠራ መኾኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሃሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለክልሎች ተላልፈው የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል እንዲያስተዳድራቸው የሚያደርግ ሥምምነት በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መፈጸሙ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰውና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርእሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ.ር) የጨበራ ጩርጩራ የዝሆን ዳና ሎጅና የሃላላ ኬላ ሪዞርት ለማስተዳደር የሚያስችል ውል መፈጸማቸውም እንዲሁ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ጎን ለጎን ቱሪዝምን ሲያስተዋውቅ መቆየቱን ገልጸዋል። አየር መንገዱ በሆቴል አገልግሎት ዘርፍም ባለ 5 ኮከብ የሆነውን የኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ገንብቶ ወደ ሥራ ካስገባበት ጊዜ አንስቶ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እየሰጠ መኾኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዚህ ቀደም ደረጃውን የጠበቀ የስካይ ላይት ሆቴሎችን በየክልሎች ለመገንባት እቅድ የነበረው ሲሆን አሁን የተገኘው አጋጣሚ ግን እቅዳችንን ”በፍጥነት እንድንተገበር አስችሎናል” ነው ያሉት።
ኢዜአ እንደዘገበው በገበታ ለሀገር ከተገነቡ ፕሮጀክቶች በስካይ ላይት ሆቴል ስር እንዲተዳደር መደረጉ የአየር ትራፖርትንና ቱሪዝምን ይበልጥ ለማስተሳሰር እድል እንደሚፈጥርም ነው የገለጹት።

በአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአምስት ዘርፍ ማለትም በመንገደኞች፣ በካርጎ በሆቴል፣ በምግብና አገልግሎት በአቪዬሽን ዩንቨርሲቲና በአውሮፕላን ጥገና አገልግሎቶች ዘርፍ እየሰራ ያለ ተቋም ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“መንግሥት ለየትኛውም የሰላም አማራጭ በሩ ክፍት ነው፣ ችግሮችን በውይይት ለመፍታትም ዝግጁ ነው” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር.)
Next articleአፍሪ ረን ጉባኤ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍን ለማጠናከር ጠቃሚ ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ገለጹ።