“መንግሥት ለየትኛውም የሰላም አማራጭ በሩ ክፍት ነው፣ ችግሮችን በውይይት ለመፍታትም ዝግጁ ነው” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር.)

58

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ አሥተዳደር ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት “ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የኅብረተሰቡ ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት ተደርጓል።

ውይይቱን የመሩት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኅላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) “በክልላችን የተፈጠረው የጸጥታ ችግር በክልሉ ሕዝብ ላይ በርካታ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰ ነው” ብለዋል።

ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ሰላሙን ለማስፈን ታላቅ ኀላፊነት አለባቸው ያሉት ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ችግሮች በውይይትና በሠለጠነ መንገድ መፈታታት እንደሚችሉ አስገንዝበዋል። ትጥቅ አንስተው የወጡ ሰዎች በሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጣ ሽማግሌ አቋቁማችሁ ሥሩ ብለዋል። “መንግሥት ለየትኛውም የሰላም አማራጭ በሩ ክፍት ነው፣ ችግሮችን በውይይት ለመፍታትም ዝግጁ ነው” ብለዋል ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)።

በውይይቱ የተገኙት የተወካዮች ምክር ቤት ባሕል፣ ቱሪዝም እና ንግድ ተቋማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አስቻለ አላምሬ “በክልሉ የፈጠረው የጸጥታ ችግር ሕዝባችንን እና ክልሉን ክፋኛ እየጎዳው ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ሰላም ሊሰፍን የሚችለው በየደረጃው ያለው ኅብረተሰብ ስለ ሰላም መዘመር ሲችል፣ ችግሮችን በውይይት እና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የመፍትሄ አካል ሲኾን ጭምር ነው ብለዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እድሚያለም አንተነህ በበኩላቸው እየደረሰ ያለውን የሰላም እጦት በቃህ ልንል ይገባል፣ ሕዝባችን የመፍትሄ አካል መኾን ይገባዋል፣ ተቀራርበን እና ተደማሞጠን ችግሩን መፍታት አለብን ብለዋል።ይህ እንዲኾንም የዞኑ አሥተዳደር የሚጠበቅበትን እና የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ሰላም እንዲሰፍን በቻልነው ሁሉ ለመሥራት ዝግጁ እንኾናለን መንግሥትም ለሚነሱ ጥያቄዎች ከመገፋፋት ወጥቶ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓልን የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ማሳለፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
Next article“የአየር ትራንስፖርትንና ቱሪዝምን ይበልጥ ለማስተሳሰር እየሠራን ነው”አቶ መስፍን ጣሰው