
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓልን ሲያከብር በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሠረት የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ እና ያለውን በማካፈል መኾን እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ መላውን የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 445ኛው ዓመተ ሂጅራ የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓል አደረሳችሁ ሲል መልዕክት አስተላልፏል። መልካም ምኞቱን ባስተላለፈበት መግለጫው ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በዓሉን ሲያከብር በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሠረት የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብ እና ያለውን በማካፈል እንዲኾን አስገንዝቧል።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ በሰጡት መግለጫ፤ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ወገኖችን፣ አቅመ ደካሞችን እና አሳዳጊ የሌላቸውን ሕጻናት በመደገፍ እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እንደዚሁም ሕዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር አንድነቱን እና ወንድማማችነቱን በሚያጠናክር መልክ በዓሉን ማሳለፍ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በመካሄድ ላይ በሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ሕዝበ ሙስሊሙ ንቁ ተሳትፎ እና ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ምክክሩ በኢትዮጵያ ታሪክ የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላት ለሕዝበ ሙስሊሙ ሁለንተናዊ መብት እና ጥቅም መከበር መልካም አጋጣሚ የሚያስገኝ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በዓሉ ከፆም እና ፀሎት ሃይማኖታዊ ሥርዓት በኋላ የሚከናወን እና በእስልምና ሃይማኖት ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው መኾኑን አስታውቀዋል፡፡
በዓሉ አሏህ የነብዩ ኢብራሂምን ፍቅር እና እምነት ፍጹምነትን ለማስተማር ልጃቸውን ለመስዋዕትነት እንዲያቀርቡ ያዘዘበት፤ እርሳቸውም ለፈጣሪ የነበራቸው እምነት እና ፍቅር ጥግ በሚያሳይ ፍጹምነት የሚወዱት ልጃቸውን እስማኤልን ወደ መሰዊያው ያቀረቡበት መታሰቢያ በዓል ነው።
ኢዜአ እንደዘገበው ፈጣሪም በልጃቸው ምትክ ለመስዋዕትነት የበግ ሙክት የላከላቸው መኾኑ የሚታወስበት በዓል ነው፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ዕለቱ የእርድ ወይም የኡዱህያ ቀን ተብሎ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበር መኾኑን አስገንዝበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!