
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ አፍሪካ ገዥው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ እና ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር አዲሱን የጥምር መንግሥት መሥርተዋል። ሲሪል ራማፎሳ ደግሞ በድጋሜ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኾነው ተመርጠዋል።
ራማፎሳ ከድሉ በኃላ ባሰሙት ንግግር መራጮች ለሁሉም መልካም ነገር እንዲመጣ እኛ መሪዎች አብረን እንድንሠራ ይጠብቃሉ ሲሉ በጥምር መንግሥቱ ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በሊቀመንበርነት የሚመሩት የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ ባለፈው ወር በተካሄደው ምርጫ አብላጫ ድምጽ አለማግኘቱን ተከትሎ ጥምር መንግሥት መመሥረት የግድ ኾኗል።
የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ የጭቆና አገዛዝ ካላቀቀ በኃላ ላለፉት 30 ዓመታት የደቡብ አፍሪካውያንን አብላጫ ድምጽ እያገኘ ብቻውን መንግሥት የመመሥረት እና የራሱን ካቢኔ የማዋቀር ዕድል አግኝቶ ቆይቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፓርቲው የሕዝብ ቅቡልነቱ እየቀነሰ መጥቷል። በሀገሪቱ እየተንሰራፋ የመጣው ወንጀል፣ ሙስና እና ሥራ አጥነት ደግሞ የቅቡልነት ማጣቱ ምክንያቶች ናቸው። በዚህ ዓመት ባለፈው ወር በተካሄደ ምርጫ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ 40 በመቶ የሚኾነውን የመራጮች ድምጽ ሲያገኝ ዲኤ የተሰኘው ተቀናቃኙ ፓርቲ ደግሞ 22 በመቶውን ድምጽ አግኝቷል። ብቻውን መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ ባለማግኘቱም ለሌሎች ፓርቲዎች የጥምር መንግሥት ምስረታ ጥሪ አቅርቧል።
ጥሪውን የተቀበሉት ዲኤ ፓርቲ እና ሌሎች ትናንሽ ድምጹን ያገኙ ፓርቲዎች ከአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ጋር ተጣምረው አዲስ መንግሥት መስርተዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!