አስሩ የዙል ሂጃ ቀናት እና የዓረፋ እለት

119

ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዙል ሂጃህ በሂጅራ የዘመን አቆጣጠር 12ኛው (የመጨረሻው) ወር ነው፡፡ በነገው እለት በዙል ሂጃ ወር በዘጠነኛው ቀን ከዒዱ ቀን አንድ ቀን በፊት በዓረፋ ተራራ ሙስሊሞች የእስልምና አስተምህሮ በሚያዘው መሰረት የአሏህን ትእዛዝ ይፈጽማሉ። የዙል ሂጃ ወር የመጀመሪያዎቹ አስር ቀናት እጅግ የተከበሩ ቀናት ናቸው፡፡ የቀናቱን ታላቅነት ከሚያመላክቱት ሃሳቦች ውስጥም፡-

አሏህ የማለባቸው መኾኑ፣ እኔን አስታውሱባቸው ማለቱ እና ከዱኒያ ቀናት ሁሉ በላጭ መኾናቸው በምክንያትነት ይጠቀሳሉ ሲሉ የእስልምና አስተምህሮቶች ይጠቁማሉ፡፡

በእነኚህ አስር ቀናት ውስጥ አላህን ማውሳት፣ ተውበት ማብዛት (ንስሀ መግባት)፣ በዒባዳ መጠናከር፣ መልካም ሥራዎችን ማብዛት፣ ከሐራም (ከሀጢአት) መቆጠብ እና ሌሎችም የቅንነት እና የአመስጋኝነት ተግባራት ይፈጸማሉ፡፡

👉ሶላት፡- በእነዚህ ቀናት ውስጥ ለፈርድ ሰላት (የግዴታ ሶላት) በጊዜ ወደ መስጂድ መሄድ፣ በፈቃደኝነት የሚሰገዱ ሶላቶችን ማብዛት የተወደደ ነው።
👉ፆም፡- በነዚህ ቀናት ውስጥ መፆም ከተቻለም ከዙል ሂጃ 1 እስከ 9 ድረስ ያሉትን ቀናት በተከታታይ መፆም፤ ለምን ቢባል ፆም በራሱ የመልካም ሥራ አካል ነውና፡፡ ከዚህም አልፎ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዘጠኙን የዙል ሂጃ ቀኖች ይፆሙ ነበር፤
👉አዝካር፡- አላሁ አክበር፣ ለኢላሃ ኢለላህ ወልሀምዱሊለህ በማለት ድምጽን ከፍ አድርገን በብዛት ማለት (ተክቢራ) ማብዛት፤
በተለይ የዓረፋን እለት መፆም፡- ረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ”የዓረፋን እለት የፆመ ሰው ያለፈውን የአንድ ዓመት እና የሚመጣውን የአንድ ዓመት ወንጀሉን ያስምርለታል ብየ እከጅላለሁ“ ብለዋል፤
👉ሃጂና ዑምራህ፡- ዑምራህ መፈጸም ቀጣዩ ዓመት ዑምራ እስኪመጣ ድረስ (በመሰል ለተፈጸሙ ጥቃቅን ኃጢአቶች) የሚያስምር ነው፤
👉ሰደቃ (ምጽዋት) ማብዛት፡- ቁርኣን መቅራትና ሌሎች ዒባዳዎችን ማብዛት የተወደደ ነው።

በሀዲስ ላይ የአላህ መልዕክተኛ ነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፤ “ከእነዚህ አስር ቀናት ይበልጥ በአላህ ዘንድ እጅግ የተከበሩ እና መልካም ሥራ ተወዳጅ የኾነባቸው ቀናቶች ፈጽሞ የሉም፤ ስለዚህ በእነሱ ውስጥ ላኢላሃ ኢለሏህ አሏሁ አክበርና አልሀምዱሊላህን አብዙ” ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደሴ ከተማ የትምህርት ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ኾኑ፡፡
Next articleበሀጅ ሥነ ሥርዓት የዓረፋ ኹጥባ