
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደሴ ከተማ ከ200 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት የትምህርት ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን የከተማ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ገልጿል። በከተማው የትምህርት ተቋማትን በማስፋፋት፣ ደረጃ በማሻሻል እና ግብዓት በማሟላት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን የትምህርት የመምሪያ ኀላፊው ፍቅር አበበ ተናግረዋል።
ከተሠሩት ውስጥ አንድ የሁለተኛ ደረጃ እና ሰባት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ትምህርት ቤቶቹም 30 መማሪያ ክፍሎች እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ሕንጻዎችን በማካተት እንደተገነቡ አመላክተዋል፡፡ ትምህርት ቤቶቹ በፈረቃ 2ሺህ 400 ተማሪዎችን ማስተናገድ ይችላሉም ብለዋል፡፡
ያረጁ ትምህርት ቤቶችን በማደስ እና ደረጃቸውን ለማሻሻል በትኩረት መሠራቱን ጠቁመዋል፡፡ በግንባታ ሂደቱ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር አውስተዋል፡፡ በደሴ የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ባዬ ይመር በሰጡት አስተያየት የትግል ፍሬ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በእርጅና ምክንያት ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
አሁን በአዲስ መልክ ሳቢ እና ደረጃውን በሚያሻሽል መልኩ መሠራቱ ልጆቻቸው በደስታ ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡ “እኛም በጉልበት እና በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የበኩላችንን ተወጥተናል” ብለዋል፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው የትግል ፍሬ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ሰሚራ ሰይድ “ትምህርት ቤታችን ተሻሽሎ በአዲስ መልክ በመሠራቱ ተደስቻለሁ” ብላለች፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!