
አዲስ አበባ: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የወራቤ ቦጆበር የ41 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራ ያለበትን ደረጃ የድርጅቱ ከፍተኛ መሪዎች በቦታው ተገኝተው ተመልክተዋል። የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በባለቤትነት እያስገነባው የሚገኘው በስልጤ ዞን ከወራቤ ከተማ ጀምሮ አሊቾ ውሪሮ ወረዳን አካቶ የሚገነባው የወራቤ ቦጆበር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ሥራ ከተጀመረ ከዘጠኝ ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡
ባለፉት ዓመታት መንገዱን እንሠራለን ብለው የገቡ ሁለት ተቋራጮች ውል በማቋረጣቸው ምክንያት የመንገድ ግንባታው እንደታሰበው ሳይኾን ሥራው በጅምር ቀርቶ እንደነበር ነው የሚገለጸው፡፡ ይሁን እንጅ በተያዘው በጀት ዓመት የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ይህን 41 ኪሎ ሜትር የወራቤ ቦጆበር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ለመገንባት ውል ወስዶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
አሁን ላይ መንገዱን በፍጥነት እና በጥራት በመሥራት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ድርጅቱ የአፈር ሙሊት፣ የውኃ ማፋሰሻ እና የስትራክቸር ሥራዎችን አጠናቅቆ አስፋልት ለማንጠፍ ዝግጁ የማድረግ ሥራዎች እንደሠራም ተገልጿል፡፡ መንገዱን በተያዘለት 24 ወራቶች ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሠራ እንደኾነ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ምክትል ሥራ አሥኪያጅ ገበያው መንግሥቴ ለአሚኮ ተናግረዋል።
ይህ በስልጤ ዞን አልቾ ወሪሮ ወረዳ ውስጥ እየተገነባ የሚገኘው የወራቤ ቦጆበር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ከዞኑ ዋና ከተማ ወራቤ መነሻውን አድርጎ መዳረሻውን ቦጆበር ከተማ የሚያደርግ የ41 ኪ.ሜ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ነው፡፡ ይህን መንገድ የአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት ውል ወስዶ ሥራውን በአጭር ጊዜ በፍጥነት እና በጥራት እየሠራ መኾኑ እንዳስደሰታቸው ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ከመላው የሀገሪቱ ክፍል በሚመጡ ሙስሊሞች በታላቅ ድምቀት የሚከበረውን የአረፋ በዓል ለማክበር ባለፉት ዓመታት መንገዱ ትልቅ ችግር ሲፈጥር መቆየቱን አንስተዋል፡፡ አሁን እየተገነባ ያለው መንግድ ችግሩን በመፍታት በዓሉን በደስታ ለማክበር ጥሩ ዕድል እንደሚፈጥርም ነው ያብራሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ሰለሞን አሰፌ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!