አሳሳቢ እየኾነ የመጣው የልብ ሕመም

38

ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የልብ ሕመም የልብ ጡንቻ፣ የልብ ቧንቧ መሸፈኛ ወይም የልብ የደም ሥሮች በተለያዩ ምክንያት ጉዳት ሲያጋጥማቸው የሚከሰት ችግር ነው። የልብ ችግር በተፈጥሮም የሚከሰት ሲኾን በሕጻናት ላይ ይበልጥ ጎልቶ እንደሚታይ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ክፍል መምህር የውስጥ ደዌ እና የልብ ሕክምና ሀኪም ዶክተር ዮሃንስ ተክለዓብ ገልጸውልናል።

የልብን ቧንቧ የሚያጠቃው የልብ ሕመም እስከ 20ዎቹ የእድሜ ክልል በሚገኙ ሰዎች ላይ በአብዛኛው ይከሰታል። የልብ ደም ሥር ሕመም ደግሞ በአብዛኛው ከአርባዎቹ የእድሜ ክልል በኋላ የሚከሰት ነው፤ አጋላጭ የኾነ ችግር ካለ ደግሞ ቀድሞ ይከሰታል። ዶክተር ዮሃንስ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ውስጥ የልብ ቧንቧ ሕመም ዋነኛ ችግር ነበር፤ አሁን ላይ ችግሩ ቢኖርም ካለፉት ሁለት 10 ዓመታት ወዲህ ደግሞ የልብ የደም ሥር ሕመም ዋነኛ የማኅበረሰብ ችግር እየኾነ መምጣቱን ገልጸዋል። በዚህ ዘገባም አሁን ላይ የማኅበረሰብ ችግር በኾነው የልብ የደም ሥር ሕመም ላይ ትኩረት አድርገናል።

የልብ የደም ሥር ሕመም በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት ላይ ተላላፊ ካልኾኑ በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እና የማኅበረሰብ ችግር እየኾነ መምጣቱን ዶክተር ዩሃንስ አንስተዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሕመሙ እንደ አደጉት ሀገራት ጥናት ባለመደረጉ የበሽታውን ሥርጭት እና የጉዳት መጠን በትክክል እንዳይታወቅ አድርጎታል።

በኢትዮጵያ ሕክምናው የሚሰጠው እንደ ጥቁር አንበሳ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ጥበበ ግዮን እና በመሳሰሉ ትላልቅ ሆስፒታሎች ብቻ ነው። በእነዚህ ሆስፒታሎች ከተመላላሽ ሕክምና እና ተኝተው ከሚታከሙ ጽኑ ሕሙማን ውስጥ የልብ የደም ሥር ሕመም ቀዳሚውን ቦታ ይይዛል፤ የብዙዎችን ሕይወትም እየቀጠፈ የሚገኝ ሕመም መኾኑንም ገልጸዋል።

የልብ የደም ሥር ሕመም በብዛት ከ40 ዓመት በላይ የእድሜ ክልል በሚገኙ ሰዎች ላይ ይከሰታል። እንደ ስኳር፣ የደም ግፊት፣ የኮሌስትሮል መጠን መጨመር፣ ከፍተኛ ክብደት፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ሲጋራ ማጨስ፣ አልኮል አዘውትሮ መጠጣት ደግሞ ለሕመሙ አጋላጭ ምክንያቶች ናቸው። በዘር እንደሚተላለፍም አንስተዋል።

እነዚህ አጋላጮች የልብ የደም ሥሮችን ብቻ ሳይኾን የኩላሊት መጎዳት፣ ስትሮክ፣ የእግር አካባቢ የደም ሥሮችን በማጥቃት ለጋንግሪን ሕመም ያጋልጣል። በአጠቃላይ በሰውነት ላይ ያሉ የደም ሥሮችን ለተለያዩ ችግሮች የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ እንደኾነ አንስተዋል።
👉ምልክቶች
ምልክቶቹ በድንገት ወይንም በሂደት ሊከሰቱ ይችላሉ። የደም ሥር እየጠበበ መምጣት፣ የድካም ስሜት፣ ትንፋሽ ማጠር፣ ደረት አካባቢ ውጋት፣ በምኝታ ወቅት ብዙ ትራስ መፈለግ የመሳሰሉ ምልክቶች ቀስ በቀስ የሚመጡ ምልክቶች ናቸው። ላብ ላብ ማለት፣ መደካከም፣መንቀሳቀስ አለመቻል የመሳሰሉ ምልክቶች ደግሞ በድንገት የሚከሰቱ ናቸው፤ ከዚህም አልፎ ድንገተኛ ሞት ሊከሰት ይችላል።
👉የሚደረጉ ምርመራዎች፦
የደም ምርመራ፣ የልብን የኤሌክትሪክ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ምርመራ፣ የልብ አልትራሳውንድ፣ ራጅ፣ ከተለመደው ራጅ ባለፈ የልብን ደም ሥሮች ራጅ መሥራት በመሳሰሉ ምርመራዎች ልብ ምን ያህል እንደተጎዳ፣ የት ላይ እንደተጎዳ፣ የመምታት አቅሙን እና የመሳሰሉ ምርመራዎች ይደረጋሉ። በምርመራ ወቅትም ተያያዥ ችግሮችንም የመለየት ሥራ ይሠራል።
👉ሕክምናው፦
የተለያዩ ሕክምናዎች እንደሚሰጡ ዶክተር ዩሃንስ አንስተዋል። የስኳር፣ የደም ግፊት፣ አላስፈላጊ ክብደትን የመሳሰሉ ለልብ ሕመም አጋላጭ የኾኑ ተጓዳኝ ችግሮችን መቆጣጠር እና ለይቶ ማከም አንዱ ዘዴ ነው። ከዚህ ባለፈ የደም ሥር ጉዳትን ተከትሎ የልብ ጡንቻ እና ቧንቧ ላይ የደረሰውን ጉዳት በመድኃኒት እና በቀዶ ጥገና (ኦፕራሲዮን) ይታከማል።
ሕክምናዎቹ ግን በኢትዮጵያ በሚፈለገው መንገድ እንደማይሰጡ ነው ባለሙያው የገለጹት። በቂ የመድኃኒት አቅርቦት አለመኖር ሌላኛው ፈተና እንደኾነም አንስተዋል። ለዚህ ደግሞ መሳሪያዎቹ እና መድኃኒቶች ውድ መኾን እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሻሻለ ቢመጣም ሕመሙን የአደጉ ሀገራት በሽታ አድርጎ የማየት ችግር ሌሎች ችግሮች ናቸው።

👉ከማኅበረሰቡ ምን ይጠበቃል?
የደም ግፊትን፣ የስኳር እና የኮሊስትሮል መጠንን እና ተያያዥ ጉዳዮችን በየጊዜው ክትትል ማድረግ እና መታከም፣ በቂ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ፣ አትክልት፣ ቅጠላቅጠል፣ ፍራፍሬ፣ ዓሣ አዘውትሮ መመገብ፣ ሲጋራ አለማጨስ፣ አልኮል አለመጠቀም፣ ሕመሙ ከተከሰተ ችግሩ እንዳይባባስ በአግባቡ ክትትል ማድረግ ይገባል።

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሕክምና እና ተሃድሶ አገልግሎት ዳይሬክተር ማረው ጌጡ (ዶ.ር) የልብ ሕክምና በክልሉ በሚገኙ የመንግሥት እና አንዳንድ የግል ሆስፒታሎች እየተሠጠ መኾኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ አገልግሎቱን ዘመኑን በሚመጥን መሳሪያ እና በሰለጠነ የሰው ኀይል የመሥጠት ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

በተለይም ደግሞ የሕጻናት ሕክምና በክልሉ ተደራሽ አለመኾኑን ነው ያነሱት። በመድኃኒት የሚደረገው ክትትል እና ቀዶ ጥገናውን ጨምሮ ሕክምናውን በክልሉ ለመስጠት የልብ ሕክምና ማዕከላት በክልሉ ለማቋቋም የሚያስችል ስትራቴጅክ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ዶክተር ማረው ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በግጭት ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመቀነስ ስለ ሰላም መወያየት ይገባል” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት
Next articleየአማራ መንገድ ሥራዎች ድርጅት የዘመናት የመንገድ ጥያቄን መፍታት የቻለ ድርጅት መኾኑን በስልጤ ዞን የአሊቾ ውሪሮ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።