“በግጭት ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርስን ጉዳት ለመቀነስ ስለ ሰላም መወያየት ይገባል” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት

34

ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶች በዜጎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያደረሱ ነው፡፡

በተለይ ሴቶች በማኅበራዊ እና በምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ተፅዕኖ ከማሳደሩ ባለፈ ለከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ይጋለጣሉ፡፡ አሁን ላይ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ የሰላም ባለድርሻ የኾኑት ሴቶች ስለሰላም መምከር እንደሚገባቸው የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢትዮጵያ ከባዱ ተናግረዋል፡፡

ሕጻናትን ለመንከባከብ እና ለማሳደግ ሴቶች ብዙ ዋጋ የሚከፍሉ ናቸው ያሉት ኀላፊዋ በሰላም እጦት እናቶች ጉዳት እየገጠማቸው ነው ብለዋል፡፡ በመኾኑም በየደረጃው በአደረጃጀት ውይይት በማድረግ ሰላምን ማምጣት ትኩረት የሚያሻው መኾኑን አስረድተዋል፡፡ ሰላሙን ለመመለስ የሴት አደርጃጀቶችን በመጠቀም ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ውይይት በክፍለ ከተሞች እና በቀበሌ ደረጃ እየተደረገ እንደሚገኝም ኀላፊዋ ገልጸዋል፡፡

ከግጭት እና ከቀውስ የሚገኝ ጥቅም እንደሌለ በመረዳት ኅብረተሰቡ ለሰላም መትጋት እንደሚገባውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የተሠራው ሥራ ውጤት አስመዝግቧል” የቱሪዝም ሚኒስቴር
Next articleአሳሳቢ እየኾነ የመጣው የልብ ሕመም