
ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሀገሪቷ የሃብት መፍጠሪያ አማራጭ እንዲኾኑ እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤት እየተመዘገበበት መኾኑን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገልጸዋል። የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
በመድረኩ ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የቱሪዝም ዘርፉ መኾኑን አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የተሠራው ሥራ ውጤት እያስመዘገበ መኾኑንም ጠቁመዋል። በውጭ ሀገር የቱሪዝም ፍሰቶችን የማስተዋወቅ እና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨመር እንዲሁም መዳረሻዎችን የማስፋት እና ነባሮችን የማደስ ሥራ ለውጤቱ መገኘት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተናግረዋል።
በተለይ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን መገንባት እና ነባሮችንም ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ በማደስ ለገበያ ክፍት በመደረጉ ዘርፉ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ቀልብ መሳብ መቻሉን ነው ያብራሩት። የኮንፍረንስ ቱሪዝምን በማስፋፋት ረገድ ባለፉት 10 ወራት በጤና፣ በትምህርት፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በሌሎችም ዘርፎች ዓለም ዓቀፍ ሥብሠባዎች እንዲካሄዱ በማመቻቸት ገቢን የማሳደግ ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል።
በርካታ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸው እና የገበታ ለትውልድ ሥራዎችን በመጀመር የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን ተሠርቷል ብለዋል። በሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች ስታንዳርድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ሊገባ መኾኑን ጠቅሰው ይህም ነባር የቱሪስት መዳረሻዎች ገበያው በሚፈልገው ልክ እንዲኾኑ ያደርጋል ነው ያሉት።
ባለፉት 100 ቀናት በሀገሪቱ ተወዳዳሪ ሆቴሎች እንዲኖሩ ደረጃዎችን የመመደብ ሥራ መሠራቱንም ሚኒስትሯ አክለዋል። ባለፉት 10 ወራት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎችን ቁጥር እና ገቢን ለማሳደግ እየተሠራ ያለው ሥራ ሚኒስቴሩ ከያዘው ዕቅድ አንጻር ውጤታማ እንደነበር አስገንዝበዋል።
ሀገሪቱ ካላት እምቅ አቅም እና ፍላጎት አንጻር ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅም ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ምቹ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ የመጓጓዣ አገልግሎት በማቅረብ የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ይሠራል ነው ያሉት፡፡ ኢዜአ እንደዘገበው ሚኒስትሯ የአገልግሎት ጥራትንም በማስጠበቅ ገቢን የማሳደግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!