
እንጅባራ: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)33ኛው የአፍሪካ የህጻናት ቀን ”የህጻናትን የትምህርት ተሳትፎ እና ጥራት የማሳደግ ጊዜው አሁን ነው” በሚል መሪ ሃሳብ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል። በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ አገዛዝን በመቃወም በ1968 ዓ.ም በሶዌቶ በተደረገ ዓመጽ የተገደሉ ህጻናትን በማሰብ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ ሰኔ 9 ቀን የሚከበረው የአፍሪካ የህጻናት ቀን ዘንድሮም በኢትዮጵያ ለ33ኛ ጊዜ በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ነው።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ሴቶች ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያም በዓሉን በፓናል ውይይት እና በተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች አክብሮ ውሏል። የብሔረሰብ አስተዳደሩ ሴቶች ህጻናት እና ማኀበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ አምባነሽ ስሜነህ በሀገራችን የህጻናት መብቶችን ለማስከበር የሚያስችሉ በርካታ የሕግ ማዕቀፎች ቢኖሩም በተለያዩ ምክንያቶች በህጻናት ላይ የሚደርሰው አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጫና ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የዘንድሮው የአፍሪካ ህጻናት ቀን መሪ ቃል በትውልድ ቀረጻ ላይ ትኩረት ማድረጉ የህጻናትን መብቶች ለማስከበር እገዛ እንደሚኖረውም መምሪያ ኀላፊዋ አንስተዋል። የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናት መብት እና ደኅንነታቸው ተጠብቆ በዕውቀት እና በሥነ ምግባር ታነፀው እንዲያድጉ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅም መምሪያ ኀላፊዋ አስገንዝበዋል።
በበዓሉ የተገኙት የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ አይተነው ታዴ ወቅቱ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲኾኑ የተደረገበት እና በከፍተኛ የሥነ-ልቦና ጫና ውስጥ የሚገኙበት ነው ብለዋል። በዓሉ ሲከበር በተለያዩ ምክንያቶች የመማር ዕድል የተነፈጋቸውን እና ለችግር የተጋለጡ ህጻናትን በመደገፍ እና በማበረታታት ሊኾን እንደሚገባም ምክትል አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
በበዓሉ ማጠቃለያ ለችግር ተጋላጭ የኾኑ ህጻናትን የትምህርት ቁሳቁስ እና የምግብ አቅርቦት ድጋፍ ተደርጎላቸዋል።
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!