“የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት በቁርጠኝነት እና በጊዜ የለንም መንፈስ መሥራት አለብን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

28

ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ)እስካሁን በተመዘገቡ ስኬቶች ሳንኩራራ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት በቁርጠኝነት እና በጊዜ የለንም መንፈስ መሥራት አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ። የ2016 በጀት ዓመት ያለፉት 10 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚ እና የዘርፎች ዋና ዋና አፈጻጸም እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኀላፊ አደም ፋራህ፣ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ.ር) ሌሎች ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና የተቋማት ኀላፊዎች ተገኝተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንዳሉት ባለፉት 10 ወራት የተመዘገቡ ውጤቶች በዓመቱ የተተነበየውን የ7 ነጥብ 9 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳካት እንደሚቻል የሚያሳዩ ናቸው።

መንግስት ኢትዮጵያ መበልጸግ አለባት የሚል ትልቅ ራዕይ ይዞ እየሠራ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንንም ማሳካት የሚያስችሉ በርካታ ምቹ ሁኔታዎች አሉ ብለዋል። የማድረግ አቅምን በመጠቀም ባለፉት ዓመታት በበጋ ስንዴ፣ በሩዝ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በኢትዮጵያ ታምርት እና ሌሎችም ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፍ የሚያስችላትን ጉዞ በአግባቡ እየከወነች መኾኗንም እንዲሁ። በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ከዓለም 57ኛ፣ ከአፍሪካ አምስተኛ እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የኢኮኖሚ ባለቤት መኾኗን የዓለም አቀፍ ተቋማት ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ ማሻገር የሚያስችሉ እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶችና አምራች ኃይል መኖሩን ጠቅሰው አመራሩም የዕይታ እና የሥራ ባሕል ለውጥ በማድረግ በትጋት መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል። በድል የመርካት እና የመጠበቅ ችግርን በመቅረፍ በሁሉም መስክ ቀጣይነት ያለው ድል ለማስቀጠል መትጋት ይገባል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር ጉዳይ በባለቤትነት መንፈስ በትብብር በመሥራት ችግሮችን በጋራ መሻገር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሀገርን ትልም ለማሳካት ምርታማነትን ማሳደግ፣ የለውጥ ሥራዎችን ማስቀጠል፣ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን በሁሉም ተቋማት መተግበር እና ሰላምን ማጽናት ቀጣይ ትኩረቶች እንደኾኑም ገልጸዋል። የ2016 በጀት ዓመት የ10 ወራት ዋና ዋና የኢኮኖሚ አፈፃፀም ሪፖርትን ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ.ር) በበጀት ዓመቱ የታቀደውን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል አመላካች ውጤቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። ለዚህም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በአገልግሎት ዘርፍ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበወረቀት እና በኦንላይን ለሚሰጠው የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
Next articleየአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ከዞኖች ጋር ወቅታዊ ሥራዎች ያሉበትን ደረጃ እየገመገመ ነው፡፡