በወረቀት እና በኦንላይን ለሚሰጠው የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

49

ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በወረቀት እና በኦንላይን የሚሰጥ መኾኑን ተከትሎ ለዚህ የሚረዳ በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። ሐምሌ መጀመሪያ አካባቢ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መሰጠት እንደሚጀመር ያስታወቁት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፈተናውን የተሳለጠ ለማድረግ ለፈታኝ መምህራን በቂ ሥልጠና እየሰተጠ መኾኑንም ገልጸዋል።

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር.) በተገኙበት ተካሂዷል። በመድረኩም የትምህርት ሚኒስቴር አፈጻጸም በስፋት ውይይት የተደረገበት መኾኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል። በ2016 በጀት ዓመት ከማኅበረሰቡ በተገኘ ድጋፍ በትምህርት ለትውልድ መርሐ ግብር 22 ሺህ የሚደርሱ የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እና ጥገና መከናወኑን አስታውቀዋል።

በተለይም ለተማሪዎች የሚሰጠው የሪሚዲያል ፈተና መጀመሩን በማስታወቅ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና መሰጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል። ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ከያዛቸው ከፍተኛ ተግባራት አንዱ በኾነው የመምህራን ሥልጠና በክረምት ወራት 62 ሺህ መምህራንን በሚያስተምሩት ትምህርት እና የማስተማር ሥነ ዘዴ ዙሪያ ሥልጠና መስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ለመምህራኑ የሚሰጠው ሥልጠና ችሎታቸውን ለማጠናከር እና ለመመዘን የሚያስችል በመኾኑ ከሥልጠናው ማጠቃለያ በኋላ ምዘናውን በብቃት ላለፉ መምህራን የሙያ ብቃት የማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል። ሚኒስቴሩ በክረምት ከያዛቸው ሥራዎች መካከል የዩኒቨርሲቲዎች ዕድሳት ሥራ አንዱ በመኾኑ ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በመጪው ዓመት ዩኒቨርሲቲዎች ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ ትምህርት እንዲጀምሩ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጸዋል። የመጽሐፍት ሥርጭትን በተመለከተ አሁን ላይ ጥምርታውን አንድ መጽሃፍ ለሦስት ተማሪ ማድረስ መቻሉን አንስተዋል።

በቀጣይ ሁለት ወራት ሚኒስቴሩ ያዘዛቸው መጽሐፍት ወደ ሀገር የሚገቡ በመኾኑ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከሞላ ጎደል ለእያንዳንዱ ተማሪ አንድ ለአንድ መጽሐፍ ማዳረስ እንችላለን ሲሉ ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ መኾን እና መልሶ ማደራጀት በተመለከተም የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አስታውቀዋል።

ከትምህርት ሚኒስቴር እንደ ተገኘው መረጃ ከዩኒቨርሲቲዎች አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እንቅስቃሴ መጀመሩን ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክክር ኮሚሽኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ትኩረት የሚሰጣቸው ዓበይት ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?
Next article“የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት በቁርጠኝነት እና በጊዜ የለንም መንፈስ መሥራት አለብን” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ