
ባሕር ዳር: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባካሄደው የምክክር ምዕራፍ አጀንዳ መሰብሰቡ የሚታወስ ነው፡፡ ኮሚሽኑ በቀጣይም ይኽንን ሂደት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እያከናወነ የሚቀጥል ይሆናል ተብሏል፡፡ ሂደቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ እየተከናወነ እንደመኾኑ ለስኬቱ ኮሚሽኑ የተለያዩ ትኩረት የሚያሻቸውን ጉዳዮች በመለየት ሥዎችን እየሰራ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡
1. አካታችነት እና ወካይነት
ኮሚሽኑ በጀመረው የምክክር ምዕራፍ በበርካታ ቡድኖች፣ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ተቋማት እና ግለሰቦች የሚቀነቀኑ የተለያዩ ሃሳቦችን በተገቢው መንገድ በማካተት ለሂደቱ ስኬት እየሰራ ይገኛል፡፡ በሂደቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአግባቡ ወኪሎቻቸውን በመላክ በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ እንዲንፀባረቅላቸው የሚፈልጓቸውን ሃሳቦች የማቅረብ መብታቸው የተጠበቀ መኾኑ ይታወቃል፡፡
2. የባለድርሻ አካላትን ኃይል ማመጣጠን
ኮሚሽኑ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የተለያየ የኃይል ሚዛን ያላቸውን ባለድርሻ አካላት እያሳተፈ እንደሚገኝ ዕሙን ነው፡፡ ይህንኑ መነሻ በማድረግ የተለያየ የኃይል ሚዛን ያላቸውን አካላት በእኩልነት እንደ ባለድርሻ አካል በመቁጠር ሂደቱን እየመራ እና እያስተባበረ ይገኛል፡፡
3. የሚቃረኑ ፍላጎቶችን ማስተናገድ
ኮሚሽኑ በሚመራው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እጅግ በርካታ ሃሳቦች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት በአጀንዳነት እየመጡ ይገኛሉ፡፡ ባለድርሻ አካላቱ የአጀንዳ ሃሳቦቻቸውን ሲያደራጁ በርካታ የሃሳብ ፍጭት ውስጥ ገብተው የተለያዩ ፍላጎቶችን እያንፀባረቁ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ኮሚሽኑ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ሃሳብ በእኩልነት የማስተናገድ ኀላፊነት ያለበት በመኾኑ ሃሳቦችን እንደአመጣጣቸው በአጀንዳነት ያስተናግዳል፡፡
4. ግልፅነት እና ህጋዊነት
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ሂደቱን የሚመለከቱ መረጃዎችን እንደ አስፈላጊነቱ ግልፅ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለሂደቱ ሕጋዊነት የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶችን አዘጋጅቶ እና በኮሚሽነሮች ምክር ቤት አስፀድቆ ሂደቱን ማስተባበር ጀምሯል፡፡
መረጃው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!