
ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 07/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓል ነብዩ ኢብራሂም የአሏህ ትዕዛዝን ለመፈጸም በፍጹም ትህትና እና ታዛዥነት ልጃቸው እስማኤልን ለመሥዋዕትነት ያቀረቡበት በዓል ነው፡፡ አሏህ የነቢዩ ኢብራሂምን መታዘዝ ተመልክቶ በምትኩ በግ እንዳቀረበላቸውም የሃይማኖቱ አስተምህሮ ያስረዳል፡፡
በመላው ዓለም የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮችም በመረዳዳት እና በመተሳሰብ በዓሉን ያከብሩታል፡፡ ድሆች እና አቅመ ደካሞችን ማሰብ እና መርዳት በሚገለጥበት በዓረፋ በዓል ለመሥዋዕትነት ከቀረበው ማካፈል እንደ ግዴታ ይቀመጣል፡፡ ይህም ደስታን የጋራ የማድረግ ኀይል እንዳለው የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ሼሪዓ ፍርድ ቤት ዳኛ ሼህ ወለላው ሰይድ እና የደብረ ማርቆስ ከተማ መስጂድ ኢማም ሼህ መሐመድ ሽፋው ይገልጻሉ፡፡
የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓል ሲከበር አንድነትን በማጠናከር ከምንም በላይ ደግሞ የእስልምና መሠረት የኾነውን ሰላምን በመጠበቅ እና ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ኀላፊነትን በመወጣት ሊኾን ይገባል ብለዋል የሃይማኖቱ አባቶች። የምሥራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ሼሪዓ ፍርድ ቤት ዳኛ ሼህ ወለላው ሰይድ የዒድ አል አድሃ ዓረፋ በዓል መተሳሰብ እና መረዳዳት በተግባር የሚታይበት በመኾኑ ሕዝበ ሙስሊሙ አቅመ ደካሞችን እና በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመርዳት እና ከጎናቸው በመቆም ሊያከብር ይገባል ብለዋል፡፡
ከራስ በላይ ለሌሎች ማሰብ በጎ ተግባራትን መፈጸም የተቸገሩ እና የተፈናቀሉ ወገኖችን በመድረስ በዓሉን ማሳለፍ ይገባል ያሉት ደግሞ የደብረማርቆስ ከተማ መስጅድ ኢማም ሼህ መሐመድ ሽፋው ናቸው፡፡ የሃይማኖት አባቶቹ በመልዕክታቸው ሀገሪቱ ካለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ እንድትወጣ ሁሉም ለሰላም እጁን እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- መልሰው ቸርነት
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!