
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ አለማጣ ወረዳ የዋጃ እና ጥሙጋ ነዋሪዎች የሕወሀትን ወረራ የሚቃወም ሕዝባዊ ሰልፍ አድርገዋል።
ነዋሪዎቹ የሕወሀት ወራሪ ኃይሎች እያደረሱት ያለውን ግፍ እና በደል በሰላማዊ ሰልፍ አውግዘዋል።
በሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፉ የተለያዩ መልእክቶችን ይዘው የወጡት የአካባቢው ነዋሪዎች እየደረሰ ያለው የማንነት ወረራ እና ትንኮሳ በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
ሰላማዊ ሰልፈኞቹ የትህነግ ታጣቂ ኃይሎች የራያን ምድር በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ እና የፌደራል መንግሥትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሕግ እንዲያስከብርላቸው ጠይቀዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ ከተሰሙት መልእክቶች መካከል፦
👉 የትህነግ ወራሪ ኃይል የራያን መሬት በአስቸኳይ ለቆ ይውጣ❗️
👉 ዛሬም ከአሸባሪነት ያልተለየው ወራሪው እና አሸባሪው ትህነግ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ኾኖ እንዲመዘገብ የሚደረገውን ሂደት አጥብቀን እንቃወማለን❗️
👉 የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በሀገር አፍራሾች አይቀለበስም❗️
👉 እኛ ራያዎች ወሎየ አማራዎች ነን❗️
👉 የፌደራል መንግሥት ለራያ ሕዝብ የማንነት ሕጋዊ ጥያቄ አስቸኳይ ምላሽ ይስጥ❗️
👉 የፌደራል መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሕግ ያስከብርልን❗️
👉 የፕሪቶሪያውን ስምምነት መንግስት ያስከብር❗️
የሚሉ መልእክቶች መስተጋባታቸውን ከሰሜን ወሎ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!