
አዲስ አበባ: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቲዎስ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን በአይነቱ የተለየ እና የትራንስፖርት ዘርፉን የሚያዘምኑ መተግበሪያዎችን አስተዋውቋል።
ድርጅቱ የኔ መኪና እና የኔ ደሊቨሪ የተሰኙ ሁለት መተግበሪያዎችን ነው ያስጀመረው።
የቲዎስ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን መሥራች ቴዎድሮስ አጥናፉ ድርጅቱ በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል ከወረቀት የፀዳ የተሽከርካሪ ቦሎ አገልግሎት እየሰጠ መኾኑን ገልጸው በይፋ አስተዋውቀዋል።
መተግበሪያዎችም በመላው ሀገሪቱ ያሉ ተሽከርካሪዎች ከወረቀት የፀዳ አሠራርን በመከተል አገልግሎታቸውን ማዘመን የሚያስችላቸው ነው ብለዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሠን በ2025 ዘርፉን ዲጂታል ለማድረግ የተሳለጠ አሠራርን መዘርጋት እንደሚገባ አንስተዋል።
በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ.ር) “መሠረታዊ የኾነውን የትራንስፖርት ዘርፍ ዲጂታል በማድረግ ሀገር የሚገባትን ጥቅም ከዘርፉ እንድታገኝ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ይገባል” ብለዋል።
ድርጅቱ ዛሬ ያስተዋወቃቸው መተግበሪያዎች የትራንስፖርት ዘርፉን ቀልጣፋ እና ዘመናዊ በማድረግ በኩል አዎንታዊ ሚና እንደሚኖራቸውም ተገልጿል።
ዘጋቢ፦ ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!