
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ11 ወራት አፈጻጸሙን ገምግሟል። የዳኞች ሥነ ምግባርን ለማሻሻል በቀጣይ ሊደረጉ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያም መክሯል።
በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር መደበኛ የዳኝነት እና የፍትሕ ሥርዓትን ለመከወን እንቅፋት ኾኖ መቆየቱ ተነስቷል።
ፍርድ ቤቱ በጸጥታ ችግር ውስጥም ኾኖ በርካታ ሥራዎችን መሠራቱም ተመላክቷል። የጸጥታ ችግሩ በሰበር ችሎት፣ በፍትሐብሔር እና የወንጀል ዳኝነት የሚቀርቡ መዝገቦች እንዲቀንሱ ማድረጉም ተገልጿል።
የቀረቡ መዝገቦች ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸሩ መቀነስ እንደታየባቸው ነው የተነገረው። የጸጥታ ችግሩ መዝገቦች ወደ ሌላ ጊዜ እንዲሸጋገሩ እና ለፍትሕ ተደራሹ እንዲዘገይ እንደሚያደርግም ተመላክቷል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዓብዬ ካሳሁን በማኅበረሰቡ ዘንድ የዳኝነት ሥነ ምግባር ችግር አለ የሚል ክስ በተደጋጋሚ እንደሚነሳ ተናግረዋል። ፍትሕ ያለ ዘመድ፣ ያለ ገንዘብ እየተሰጠ አይደለም የሚል ክስ መኖሩንም ገልጸዋል። ነገር ግን መላ ሥርዓቱን ከመተቸት ያለፈ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ችግር የሚፈጥሩ አካላትን ለይቶ የመስጠት ውስንነት አለ ነው ያሉት።
ዳኝነት ከሙያዎች ሁሉ የላቀ ሥነ ምግባር የሚጠይቅ ሙያ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዳኝነት ሥርዓቱ የሚነሱ ችግሮችን ለማስተካከል የመፍቻ ስልቶችን ቀይሶ መሥራት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል። ሙያዊ ሥነ ምግባርን አክብረው ለሕዝብ እውነተኛ ፍትሕን የሚሰጡ ዳኞችን ሥነ ምግባር ከጎደላቸው ጋር ሊለይ የሚችል አሠራር እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
ክልሉ የጸጥታ ችግር ውስጥ ቢቆይም በችግር ውስጥ ኾኖ ባለጉዳይ ይመጣ እንደነበር ነው የተናገሩት። ዳኞችም የመጡትን ባለጉዳዮች ሲያስተናግዱ መክረማቸውን ነው የገለጹት። ባለጉዳዮችን በተሟላ መንገድ ለማስተናገድ የጸጥታ ችግሩ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩንም አንስተዋል። የተሠራው ሥራ ክልሉ ከነበረበት ሁኔታ አንፃር መልካም እንደኾነም ገልፀዋል።
በችግር ውስጥ ኾነን አገልግሎት ሰጥተናል፣ የዳኝነት እልባትም ሰጥተናል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ። በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ያልተመለሱ መዝገቦች ወደፊት እንደሚንከባለሉም ገልጸዋል። በፕላዝማ ተደራሽ ለመኾን ጥረት መደረጉን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ፕላዝማዎች ሊሠሩ ባለመቻላቸው የሚፈለገውን ያክል መሥራት አለመቻሉን ተናግረዋል።
ቀጠሮው እየተራዘመ ወደሚቀጥለው ሲሸጋገር የሚፈጠረውን ጫና ለመቀነስ ስልት ነድፎ መሥራት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። መዝገቦችን በፍጥነት ማየት፣ የዳኞችን ቁጥር መጨመር፣ መሪዎች ተገቢውን ክትትል ማድረግ ጫናውን ይቀንሰዋል ነው ያሉት።
የዳኝነት ሥነ ምግባርን እና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ በእቅዳችን ውስጥ አንዱ ግብ ተደርጎ ጥረት የሚደረግበት ሥራ ነው ብለዋል።
የዳኝነት ሥነ ምግባርን እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተቋቀሙ ተቋማዊ አደረጃጀቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል። ተቋማዊ አደረጃጀቶቹ ናሙናዎችን በመውሰድ እና አቤቱታ ሲመጣ በመመርመር እና በማጣራት በተገኘበት ላይ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ሢሠራ መቆየቱን አንስተዋል። ከዚህ ባለፈ የሥነ ምግባር ጉድለቶችን ማሻሻል የሚያስችሉ ሥልጠናዎች ለዳኞች ሲሰጡ እንደነበር ገልጸዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም በዳኝነት ሥራው ውስጥ ያለውን አሉባልታ እውነታነት ለማረጋገጥ መጠይቆችን በማዘጋጀት የጥቆማ ሥርዓቶችን ተከትሎ መረጃ ለማሰስ እና እውነታውን ለማረጋገጥ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በሚደረገው መጠይቅ፣ ጥቆማ እና የምርምራ ሥራ ጥፋተኛ ኾኖ የሚገኝን ዳኛ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችል መንገድ መኖሩን ነው የተናገሩት።
አካሄዱ በሥነ ምግባር ብልሹነት ውስጥ የሚገኙ ጥቂት ዳኞችን ለመለየት እንደሚያስችልም ገልጸዋል። ውይይት ከተደረገበት በኋላ መጠይቅ ተበትኖ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የተሰበሰቡትን መተንተን፣ የሚተነተኑትን እየመረመሩ ወደ ማጣራት የመሄድ ሥራ እናከናውናለን ነው ያሉት። ሥራው ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መኾኑንም ገልጸዋል። ሂደቱ የሚፈጸመው በጥንቃቄ እና በምስጢር መኾኑንም ተናግረዋል።
ማኅበረሰቡ እውነትን ይዞ መጠይቁን በመሙላት እና ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበርም ጥሪ አቅርበዋል። ሂደቱ ሰውን የመጉዳት ሳይኾን ሥርዓቱን አጥርቶ ተገቢውን አገልግሎት የመስጠት ዓላማን ያነገበ ነው ብለዋል። ዓላማውን ለማሳካት ደግሞ የማኅበረሰቡን እውነተኛ ተሳትፎ ይፈልጋል ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ከተባባረ እውነቱ ሊወጣ እንደሚችልም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!