
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የክልል እና የፌደራል ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በወልዲያ ከተማ ተገኝተው በከተማ አሥተዳደሩ በጀት የሚሠራውን የ30 ሜትር ስፋት ያለውን የቀለበት መንገድ ሥራ ተመልክተዋል።
የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) የ30 የመንገድ መሠረተ ልማቱ ከተማዋን ሙሉ በቀለበት የሚያስተሳስር፤ የከተማዋን አማራጭ መንገዶች የሚያሰፋና የከተማዋን የወደፊት ራዕይ ታሣቢ በማድረግ የተሠራ ነው ብለዋል።
የከተማ አሥተዳደሩ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ቢሆንም ለሕዝቡ የሚሠሩ ሥራዎችን ማስተዋወቅ ላይ ውስንነት እንዳለም ገልጸዋል።
ምሥራቁን ከምዕራብ፣ ሰሜኑን ከደቡብ በምታገናኘው ታዳጊ በሆነችው የመገናኛዋ ከተማ ወልድያ በሀገራችን ያሉ ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉና ኢንቨስት ያደረጉትም ወደ ሥራ እንዲገቡም ዶክተር መንገሻ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው፤ የመንገዱ ሥራ አፈጻጸሙ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑንና በሥራው የማኅበረሰቡን ተሳትፎ በማጠናከር የቀለበት መንገዱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲከናወን እንደሚሠራ ገልጸዋል። መረጃው የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ኮምዩኒኬሽን ነው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!