
ደሴ: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመጭው የክረምት ወቅት በሚኖረው የአየር ጠባይ ትንበያ ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በደሴ ከተማ ተካሂዷል። በባለፉት አራት ወራት የበልግ ወቅት በምሥራቅ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ስር ባሉት የሰሜን ወሎ፤ የሰሜን ሸዋ፤ የደቡብ ወሎ፤ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና የዋግኽምራ አካባቢ ያለውን የአየር ትንበያ ሁኔታ እና ውጤት በመድረኩ ለተሳታፊዎች ቀርቧል።
ባሳለፍነው የበልግ ወቅት በአብዛኛው የምሥራቅ አማራ አካባቢ መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን እንደነበራቸውም መረጃዎች ያመለክታሉ። የምሥራቅ አማራ ሜቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ከእርሻ፣ ከውኃ እና ከጤና አኳያ የበልግ ወቅት ዝናብ የነበረው በጎ እና መጥፎ ተጽዕኖዎች እንደነበሩትም ተዳስሷል።
በክረምቱ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ትንበያው የሚያሳይ በመኾኑ የተሻለ እርጥበት እና ውኃ ለማግኘት የሚያስችል መኾኑንም የምሥራቅ አማራ ሜቲዎሮሎጅ አገልግሎት ማዕከል ዴስክ ኀላፊ እንዳላማው ወንዴ ገልጸዋል። የምሥራቅ አማራ ሚቲዎሮሎጂ ማዕከል መሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ይመር መሐመድ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ያለው የመረጃ ልውውጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያብራሩት።
የጎርፍ አደጋ እንዳይደርስ ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው ሲሉ የምሥራቅ አማራ የሜትዎሮሎጂ ማዕከል የትንተና እና ትንበያ ባለሙያ ሉባባ መሐመድ አብራርተዋል። ለአሚኮ ሃሳብ የሰጡ ተሳታፊዎችም ከተቋሙ ጋር የመረጃ ልውውጥ ማድረጋቸው ለአርሶአደሩ ተገቢውን መረጃ ለመስጠት እንደሚረዳቸው አስረድተዋል። በመድረኩ ከተለያዩ ዞኖች ከጤና፣ ከግብርና እና ከአደጋ መከላከል መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳታፊ ኾነዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሐመድ በቀለ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!