
ባሕር ዳር: ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመጭው ክረምት ወራት ከመደበኛ በላይ የዝናብ ሥርጭት እንደሚኖር የምዕራብ አማራ ሚቲዮሮሎጅ አገልግሎት ማዕከል ገልጿል። በኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጅ ኢንስቲትዩት የምዕራብ አማራ ሚቲዮሮሎጅ አገልግሎት ማዕከል የ2016 ዓ.ም የበልግ አየር ጠባይ ግምገማ እና የ2016/17 ዓ.ም የክረምት ወራት የአየር ጠባይ ትንበያን አስመልክቶ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል።
የምዕራብ አማራ የሚቲዮሮሎጅ አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር ሲሳይ ቀለሙ በበልግ ወቅት የዝናብ ሥርጭት እና መጠን መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ እንደነበር ገልጸዋል። አልፎ አልፎም የዝናብ እጥረት እንደነበርም አንስተዋል። በመጭው የክረምት ወራትም መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የኾነ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ገልጸዋል።
በዚህም ለጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ተጋላጭ በኾኑ አካባቢዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። በተለይም በከተሞች አካባቢ የውኃ ተፋሰስ ቦታዎችን ማጽዳት፤ ተፋሰስ በሌላቸው አካባቢዎች ደግሞ ማዘጋጀት እንደሚገባ አሳስበዋል። በአንድ አንድ አካባቢዎች ደግሞ እንደ ባለፈው ዓመት የዝናብ እጥረት እንደሚኖር ያነሱት ዳይሬክተሩ ቀድሞ ውኃን የማሰባሰብ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ተቋማትም ይህንን ተገንዝበው ቅድመ ዝግጅት በማድረግ የሚጠበቅባቸው ሥራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል። የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሰብል ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ.ር) እንዳሉት በበልግ ወራት በነበረው በቂ የዝናብ መጠን የሚታረሰውን የመሬት መጠን 5 በመቶ፣ የዘር ሽፋን ደግሞ 3 በመቶ ማሳደግ ተችሏል።
በየጊዜው የሚደረጉ የአየር ትንበያዎች የግብርና ሥራውን በተለይም ደግሞ የሰብል ልማት ምርታማነትን ለማሳደግ እና ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከል እንደ ግብዓት ያገለግላሉ። በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተቋም ምክትል ዲን ተባባሪ ፕሮፌሰር ደጀኔ ሳህሉ የአየር ትንበያውን መንግሥታዊም ኾነ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በመውሰድ ሊከሰት ለሚችል ማንኛውም ችግር ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት ያስፈልጋል። ዩኒቨርሲቲውም ለተቋማት ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ ምክትል ዲኑ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!