የመንግሥት ተቋማት አገልግሎትን ወደ ኤሌክትሮኒክ ወይም ዲጀታል ሥርዓት ለማስገባት በትኩረት እየተሠራ መኾኑ ተገለጸ።

16

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ.ር.) የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማፋጠን በተሠሩ ሥራዎች እስካሁን 620 ሀገራዊ የመንግስት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል ሥርዓት ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር.) በተገኙበት የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።

በመድረኩ ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መኾኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ.ር.) ገልጸዋል። ከሚኒስቴሩ ቁልፍ ተልዕኮዎች አንዱ የዲጂታላይዜሽን ትግበራውን ማፋጠን እና ማስፋፋት መኾኑን አንስተዋል።
የዲጂታል ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ተቀርጾ የመንግሥትን ተቋማት አገልግሎት ወደ ኤሌክትሮኒክስ ወይም ዲጀታል ሥርዓት ለማስገባት ትኩረት ተደርጎ መሠራቱን ገልጸዋል።

እስካሁን 620 ሀገራዊ የመንግሥት አገልግሎቶች በዲጂታል ሥርዓት እንዲገቡ መደረጉንም ጠቁመዋል። በቀጣይም የመንግሥት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል ሥርዓት የማስገባት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ቴሌኮምን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሀገራዊ የዲጂታል እንቅሰቃሴ ከፍተኛ እምርታ የመጣበት መኾኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን ከስድስት ትርሊዮን ብር በላይ በዲጂታል ፋይናንስ እንቅሰቃሴ መደረጉን ተናግረዋል።

የዲጀታል ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግም በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት። ሚኒስቴሩ በኢኖቬሽን እና ምርምር ዘርፍ ረገድ በጤና፣ በማምረቻ፣ በግብርና እና በሌሎችም ዘርፎች ችግር ፈቺ የኾኑ የምርምር ውጤቶችን ተደራሽ የማድረግ እና ቴክኖሎጂ የማላመድ ሥራዎችን ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ማከናወኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም የስታርአፕ ምሕዳሩን ለማስፋት በተሠሩ ሰፋፊ የድጋፍ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል። በተጠሪ ተቋማት በኩል ከሚሠሩ የምርምር ሥራዎች አንጻርም መልካም ውጤቶች እንደተገኙ በግምገማ እንደተረጋገጠ አንስተዋል። የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ማድረግ የሚያስችሉ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች እና በክህሎት ተኮር የዲጂታል ልማት ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አስታውቀዋል።

ሚኒስቴሩ በቅርቡ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የዲጂታል ክህሎት አቅም ለመገንባት በመጀመሪያ ዙር 10 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ኤኒሼቲቭ መጀመሩን ገልጸዋል። ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን እውን ለማድረግ ወጣቶች ላይ መሥራት ወሳኝ ጉዳይ በመኾኑ እስከ አንድ ሚሊዮን ወጣቶችን በዚኽ ኢኒሼቲቭ ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት እንደሚቀጠልም አረጋግጠዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች ተፈላጊውን ክህሎት እንዲጨብጡ በትኩረት እየተሠራ ነው።
Next article“በአማራ ክልል ያለው የፋይናንስ አካታችነት ማዕቀፍ አሁን ካለበት 35 በመቶ ወደ 70 በመቶ ለማሳደግ እየተሠራ ነው” ብሔራዊ ባንክ