
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንደተናገሩት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች ተፈላጊውን ክህሎት እንዲጨብጡ የማብቃት ተግባር ትኩረት ተሰጥቶታል። በ2016 በጀት ዓመት ባለፉት አስር ወራት ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ሚኒስትሯ ተናገረዋል።
በተለይም የሠለጠነ የሰው ኃይል ወደ ውጭ ለማሠማራት አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው ሥልጠና ከመስጠት ባለፈ ብቁ ስለመኾናቸው የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል። እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ በበጀት ዓመቱ አስር ወራት 314 ሺህ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ኾነዋል።
የሥራ ስምሪቱ ዜጎች ደኅንነታቸው፣ ጥቅማቸው እና መብታቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ በሚያስችል መልኩ መከናወኑንም አብራርተዋል። በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መኾናቸውን ጠቅሰው በጥቅሉ ለ3 ሚሊዮን 77 ሺህ ዜጎች የሀገር ውስጥ እና የውጭ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ እንዳሉት የዲጂታል ሥርዓት በመዘርጋት ዜጎች ተመዝግበው ወደ ሥራ ገበያው እንዲገቡ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይም በትኩረት እየተሠራ ነው። በቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍም ወጣቶች ያላቸውን የፈጠራ ሀሳብ ወደ ቴክኖሎጂ ምርት መቀየር የሚችሉበት ሥልጠና እና ምቹ ምሕዳር መፈጠሩንም አክለዋል።
በዚኽም የሥራ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶችን በማወዳደር ምርቶቻቸውን ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት እንዲጠቀሙ በተጀመረው ሂደት 76 ቴክኖሎጂዎች ወደ ምርት መሸጋገራቸውን አብራርተዋል። ኢፕድ እንደዘገበው ስታርትአፖች እና ኢንተርፕራይዞችን በማጎልበት ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ በመንግሥት ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!