
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሰኔ ሰማይ ሲጠቁር፣ ደመናው ዝናብ እያዘለ ሲያንዣብብ፣ ዝናብ የተሸከመው ዝናብ የያዘውን ሲለቅ፣ ዶፍ ሲወርድ፣ ጎርፍ ከዳር ዳር እያማታ ሲገማሸር፣ ልባቸው የሚሰጋ፣ የት ልከርም ነው? ምን ሊበጀኝ ነው? ልጄቼን የት ልጣላቸው? ከየት አስጠልዬ ላክርማቸው? ክረምቱ አልፎ ፀሐይ የምትወጣው መቼ ይኾን? እያሉ የሚጨነቁ እናቶች ብዙ ናቸው።
ገሚሶች በተመቻቸ ቤት፣ የጣፈጠ በልተው እና ጠጥተው፣ በተመቻቸ አልጋ ላይ ተኝተው፣ በክረምቱ መግባት፣ በዝናቡ አወራረድ ሀሴት ሲያደርጉ፣ ብዙዎች ደግሞ በተቀደደች ጣሪያቸው ሥር የምትፈስሰው ዝናብ ከልጆቻቸው ላይ እንዳትወርድባቸው፣ የቤታቸውን እቃ፣ የእለት ጉርሳቸውን እንዳታበላሽባቸው፣ የዝናብ ማጠራቀሚያ ሲያስቀምጡ፣ ቀዳዳውን ሲደፍኑ፣ ሰዓት ሲቆጥሩ ያድራሉ።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 16 የአቅመ ደካሞችን ቤት ጥገና እና ግንባታ በማስጀመር የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት አስጀምረዋል። እርሳቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማስጀመሩበት አካባቢ መውጫ መግቢያ የሌላቸው፣ በበጋ ፀሐዩ፣ በክረምት ዝናቡ የሚያገኛቸው ደሳሳ የአቅመ ደካማ ቤቶች በስፋት ይታያሉ።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የቤት እድሳት ከተጀመረላቸው አንዷ ዘይንያ አንተነህ ናቸው። እርሳቸው እርጅና በተጫጫናት፣ ተጫጭኖ ባዘመማት፣ ዝናብ በሚገባባት፣ ፀሐይ በሚፈራረቅባት ቤት ውስጥ ይኖራሉ። የቤታቸው ዘማማነት እና ለመውደቅ መድረስ ደግሞ ለሕመማቸው ምክንያት እና መባባስ እንደኾነች ነው የሚናገሩት።
በደሳሳ ጎጆ በአስም እየተሰቃየሁ እስከዛሬ ኖሪያለሁ፣ አሁን ስለመጡልኝ አመሰግናለሁ፣ አላህ ይስጥልኝ ነው ያሉት። የጎርፉ እና የዝናቡ ችግር ለበሽታ ዳርጓቸው እንነበርም ነግረውናል። ከአሁን ቀደም የነበረችው ደሳሳ ጎጇቸው ከላያቸው ላይ ልትወድቅ ደርሳ የት በገባሁ እያሉ ሲጨነቁ እንደነበር ነው የገለፁት። ከበአድ ከዘመድ ብዬ ያሠራኋት ቤት ከላየ ላይ ወድቃ ነበር፣ ማን በሠራልኝ ስል አላህ አመጣልኝ፣ ደረሱልኝ ብለዋል።
ሌላኛዋ እናት ገበያነሽ ኢብራሂም ዱር እና ዋሻ በመሰለች ቤት ኖሪያለሁ፣ ልጄቼን ግራምጣ እየሰፋሁ አሳደኩ፣ ቤት ከላይ እየወደቀብኝ ነው ያሉት። አሁን ቤቴ ሊሠራ ስለተጀመረ እድለኛ ነኝ፣ ደስም ብሎኛል። አመሰግናቸዋለሁ፣ ሀገሩን ሰላም ያደርገው ብለዋል። እሳቸው ያለቀሱባቸው፣ አምላካቸውን ያማረሩባቸው፣ ተስፋ አጥተው አብዝተው ያዘኑባቸው ጊዜያት እንደነበሩም ነግረውናል። ልጆቼን ከወለል ላይ ሰብስቤ ነው የምተኛው ዝናብ እና ብርድ ሲመጣ የምደርስበት እየጠፋኝ እንቅልፍ ሳልተኛ ይነጋም ነበር ነው ያሉት።
የሀገሬው ሰው ደመናው ሲመጣ፣ መሬት ዘር ትሰጣለች፣ በልምላሜም ትመላለችና ደስ ይለዋል። እንደ ወይዘሮ ገበያነሽ ያሉ ቤታቸው የዘመመባቸው፣ ቀዳዳዋ የበዛችባቸው አቅመ ደካሞች ግን በደመናው መምጣት ይሸበራሉ፣ ያዝናሉ፣ ይተክዛሉ፣ ሰማዩ ባጉረመረመ ቁጥር የት እከርም ይኾን? እያሉ ይደነግጣሉ።
ደመናው ሲመጣ ጌታ ፈጣሪዬ ኾይ ዝናቡን ያመጣኸው የት ልተኛ ነው? ዝናብ ያመጣኸው የት ልወድቅ ነው? የትስ ገብቼ ልከረም? ለምን ተውከኝ? እያልኩ አለቅሳለሁ፣ ባለቤቴ ደካማ የጤና እክል ያለበት፣ ልጆቼም የጤና ችግር የገጠማቸው ናቸው፣ የረሃብ የጥም፣ የሀዘን ዘመን አሳልፌያለሁ፣ በችግር ውስጥ ኖሬያለሁ ነው ያሉት። አኹን እንኳን ቤቴ ይሠራልኝ እንጂ ለሆዴስ አላንስም ብለዋል። ስንት መከራ አሳለፍኩ መሰላችሁ፣ አሁን ደስ ተሰኝቻለሁ። ሀገሬን ሰላም ያድርጋት እንጂ ይላሉ።
ወይዘሮ ገበያነሽ በዚያች ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ልጆቻቸውን በመካራ ውስጥ ኾነው እንዳሳደጉ ነው የነገሩን። ቀሚሴን ከሁለት እየቀደድኩ እያለበስኩ ልጄቼን ወለል ላይ አስተኛለሁ፣ እኔ ደግሞ ከመሃላቸው ቁጭ ብዬ፣ ለእለት ጉርስ የማገኝባትን ስፌት ስሰፋ አድራለሁ፣ ምን ይነገራል ያሳለፍኩት የችግር ጊዜ፣ ምን ይወራል፣ እንኳን ጸሐይ ወጣች፣ እንኳን ለዚህ ደረስኩ ነው ያሉት።
በዚያች ሠፈር ለተመላለሰ ሰው ከንፈሩን የሚመጥባቸው፣ ዓይኖቹ እንባን የሚያቀሩባቸው፣ ልቡ በሀዘን የምትሰበርባቸው የበዙ የችግር አኗኗሮችን ያያል። መጸዳጃ ቤት የሌላቸው ለመኖር አይደለም አንድም ጊዜ ደርሶ ለመመለስ የሚከብዱ ቤቶችን ያያሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!