“ውስጣዊ ችግሮቻችንን ባለመቅረፋችን ምክንያት ተጋላጭነታችን ጨምሯል” ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)

30

ደሴ: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር “ለዘላቂ ሰላም እና ልማት ግንባታ የወጣቶች ሚና” በሚል መሪ መልዕክት ከወጣቶች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው። የውይይቱ ተሳታፊ የከተማዋ ወጣቶች በሃሳብ የበላይነት ማመን ለሰላም መስፈን ቁልፍ መኾኑን ጠቁመዋል።
የጦርነትን አስከፊነት ስለምናውቀው የክልሉም ኾነ የፌዴራል መንግሥት የተፈጠረውን ችግር ከጠመንጃ ውጭ እንዲፈታ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።

በሌላ በኩልም ወጣቱ ለእኩይ ዓላማ ማስፈፀሚያ እንዳይኾን ሥራ ሊፈጠርለት ይገባል ያሉት ወጣቶቹ በከተማዋ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች መልካም የሚባሉ ቢኾኑም ብዙ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ከወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ባለፈ በከተማዋ ያሉ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱም ጠይቀዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መሀመድአሚን የሱፍ የኮምቦልቻ ከተማ ሰላሟን አስጠብቃ እንድትቆይ የወጣቶች ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር ጠቅሰው ምሥጋና አቅርበዋል። አሁን ላይ በክልሉም ኾነ በሀገሪቱ የተፈጠሩ ቀውሶች ኢትዮጵያ የብዝኃ ሀገር መኾኗን ካለመረዳት የመነጨ ነው ብለዋል።
ለዚህም እንደወጣት ሁሉንም ብሔር፣ ሃይማኖት እና የፖለቲካ አመለካከት ማክበር እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፈ እንድሪስ አብዱ ኢንቨስትመንት ከሚገመገምባቸው መስፈርቶች አንዱ ምን ያህል የሥራ ዕድል ይፈጥራል የሚል እንደኾነ ጠቅሰው በኮምቦልቻ ከተማ የወጣቱ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከከተማ አሥተዳደሩ እና ከአልሚዎች ጋር እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጄኔራል አሰፋ ቸኮል ኢትዮጵያ መንግሥት የሌላት ሀገር ኾና ማየት የሚፈልጉ ውስጣዊ እና ውጫዊ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ሀገር ተከብሮ እንዲኖር ማድረግ ለአንድ ግለሰብ ወይም ተቋም የሚተው ስላልኾነ ወጣቱ የድርሻውን መወጣት እና ሌሎችም ወደ ሰላም እንዲመጡ ጥሪ ማቅረብ ይኖርበታል ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) “ውስጣዊ ችግሮቻችንን ባለመቅረፋችን ምክንያት ለችግሮች ተጋላጭነታችን ጨምሯል” ነው ያሉት። በሁሉም አካባቢ ያሉ ወጣቶች ስለጽንፈኛው ቡድን እና ስለክልሉ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ማወቅ እና መረዳት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

በየአካባቢው ከጸጥታ መዋቅር ነፃ የኾነ ሰላምን መፍጠር ካልተቻለ አሁን ያለውን ሁኔታ መቀልበስ ስለማይቻል ወጣቱ ያለውን አቅም እና ጉልበት ተጠቅሞ ሰላምን ማስፈን እንደሚገባውም ጠቅሰዋል። ከሌሎች ወንድም እና እህት ሕዝቦች ጋር በመኾን የአማራ ሕዝብ ጥያቄ እንዲፈታ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም ነው ያስገነዘቡት።

ዘጋቢ፡- መስዑድ ጀማል

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በክልሉ መንግሥት የጥርሀሆ ድልድይ በመገንባቱ የአካባቢው ነዋሪዎችን የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ
Next article“ባለፉት 10 ወራት 129 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ገብተዋል” የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል