
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በምሥራቅ በለሳ ወረዳ የጥርሀሆ ወንዝ ድልድይ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ኹኗል። የድልድዩ መገንባት ከፍተኛ የኾነ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ከዚህ በፊት በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ እንግልት ያደርስ የነበረው የጥርሀሆ ወንዝ በክልሉ መንግሥት በጀት 29 ሚሊዮን 788 ሺህ 589 ብር በኾነ ወጪ ድልድይ ተገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ በመኾኑ ለማኅበረሰቡ ጥያቄ ምላሽ አስገኝቷል።
የወረዳው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት የጥርሀሆ ወንዝ በክረምት ወቅት ከአቅም በላይ ስለሚሞላ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ተጽእኖ ሲያሣድር መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በወንዙ ላይ የተገነባው ድልድይ ክረምት ሲመጣ ወንዝ ለመሻገር ያለባቸውን ስጋት መቅረፉንም ተናግረዋል፡፡
የድልድዩ ተጠቃሚዎች የድልድዩ መገንባት በፈለጉት ሰዓት ያለ ስጋት ወደ ገበያ ለመሄድም ኾነ ዘመድ ለመጠየቅ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ ኃላፊ አስንቃ ክብካብ የምሥራቅ በለሳ ወረዳ ሕዝብ ላለፉት በርካታ ዓመታት በመንገድ መሠረተ ልማት እጦት ሲቸገር መቆየቱን ነው የተናገሩት። አሁን ላይ በክልሉ መንግሥት የጥርሀሆ ድልድይ በመገንባቱ የአካባቢው ነዋሪዎችን የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነውም ብለዋል።
የድልድዩ መገንባት የአካባቢውን ነዋሪዎች ከስጋት ነፃ ያደረገ እንደኾነ ያብራሩት ወይዘሮ አስንቃ ክብካብ ድልድዩ በርካታ ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ከማድረጉ በተጨማሪ ለዞዝ-አምባ ጊዮርጊስ የቱሪዝም ፍሰት ፋይዳው የጎላ ነው ማለታቸውን ከዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የጥርሀሆ ወንዝ ድልድይ ጎሀላ ከተማን ከዞዝ-አምባ ቀበሌ የሚያገናኝ ሲኾን በዓባይ ግድብ ተቋራጭ ኅብረት ሥራ ማኅበር አማካኝነት ሺገነባ ሽሎ አማካሪ የባለሙያዎች ማኅበር ደግሞ የማማከር ሥራውን ሠርቷል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!