“ብቁ እና ጤናማ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር የከተሞቻችንን ጽዳት መጠበቅ ልምድ ማድረግ ይኖርብናል” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)

50

ደብረ ብርሃን: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጽዱ አካባቢን ለመፍጠር በሀገር አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡ ጽዱ አካባቢ እና ጽዱ ጤና ተቋም ለተሟላ ጤንነት በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ብርሃን ከተማ የጽዱ ከተማ ሥራ ተጀምሯል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) “ብቁ እና ጤናማ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር የከተሞቻችንን ጽዳት መጠበቅ ልምድ ማድረግ ይኖርብናል” ብለዋል፡፡

ደብረ ብርሃን ከተማ የዕውቀት እና የኢንዱስትሪ ከተማ ናት ያሉት ዶክተር አሕመዲን በተለያዩ ተቋማት ላይ እየተጀመሩ ያሉት የጽዳት ተግባራት ተስፋፍተው ሁሌም ልምድ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ደብረ ብርሃን ከተማ ሦስት መሠረታዊ ተግባራትን ትፈልጋለች ያሉት ዶክተር አሕመዲን ሰላም፣ የነቃ ማኅበረሰብ እና ልማት ያስፈልጓታል ነው ያሉት፡፡

ጽዱ አካባቢን መፍጠር ዓላማ ያደረገው መርሐ ግብር በደብረ ብርሃን ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተጀመረ ሲኾን የጤና ተቋማት የሚያከናውኑት የጽዳት ተግባር ጥቅሙ የጎላ ስለመኾኑም ተነስቷል፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ በቀለ ገብሬ በከተማው ያሉ ሁሉም የጤና ተቋማት ዘመቻውን ተቀላቅለው ጽዱ ተቋም እንዲኖራቸው በትኩረት እየተሠራ ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡

የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት ደብረ ብርሃን ከተማ በብዙ መንገድ እየተለወጠች ያለች ከተማ መኾኗን አንስተዋል፡፡ ቀጣይነት ያለው እድገቷን አሁንም ለማስቀጠል ጽዱ ተቋማት እና ጽዱ ከባቢ እንደሚያስፈልግ በማመን ከተማ አሥተዳደሩ ሥራዎችን እየሠራ ስለመኾኑ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ወንዲፍራ ዘውዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል መጠነኛ የገበያ መረጋጋት መኖሩን የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
Next article“በክልሉ መንግሥት የጥርሀሆ ድልድይ በመገንባቱ የአካባቢው ነዋሪዎችን የዘመናት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው” የማዕከላዊ ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ