ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ እና ሥነ-ጥበብ የፈጠራ እና ትዕይንት ውድድር ሊካሄድ ነው፡፡

49

አዲስ አበባ: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “የባሕል ጥበባት ለማኅበረሰብ ትስስር እና ለሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ እና ሥነ ጥበብ የፈጠራ እና የትዕይንት ውድድርን አስመልክቶ ባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር ከሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ የኪነ ጥበብ፣ ሥነ ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ “እንደዛሬው ቴክኖሎጂ ባልተስፋፋበት ዘመን የቀደሙ አባቶች ተፈጥሮ የሠጠቻቸውን ጥበብ ተጠቅመው ሀገርን አቆይተዋል” ብለዋል። ጥበብ በአንድ ሀገር ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ የሚገኝ መኾኑን እና ብሔር፣ ሃይማኖት እንዲሁም ዕድሜ የማይገድበው ለሁሉም የተሠጠ ስጦታ መኾኑን አንስተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ “ሚዲያዎች ያሉንን ባሕል እና ጥበብ የምንሸጥባቸው ናቸው” ብለዋል፡፡ ኪነጥበብ እና ሚዲያ አብረው የሚሄዱ መኾናቸውን በመገንዘብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው ውድድር የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል። በውድድሩ አራት ጉዳዮች ሲካተቱ ሙዚቃ፣ ስዕል እና ፋሽን ሾው ውድድር የሚደረግባቸው ዘርፎች ናቸው ተብሏል። በትዕይንት ደረጃ ደግሞ ኢግዚቢሽን እንደሚዘጋጅ ታውቋል።

በዚህ ውድድር 14 ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ አሥተዳደሮች ይሳተፉበታል ተብሏል። ይህ ውድድር በየዓመቱ በዙር የሚከናወን ኾኖ የመጀመሪያው ውድድር አዲስ አበባ ላይ ይከናወናል፡፡ ውድድሩ በሌሎች ክልሎችም ተደራሽ እንደሚኾን ይጠበቃል። በመድረኩ የመወያያ ሠነድ ቀርቦ ውይይት ተካሄዶበታል።
ውድድሩ ከሰኔ 13/2016 ዓ.ም እስከ ሰኔ 15/2016 ዓ.ም ለማካሄድ መርሐ ግብር ወጥቶለታል።

ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ኃይለኢየሱስ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአቢሲኒያ ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀውን አሚን አዋርድ የሥራ ፈጠራ ውድድር ይፋ አደረገ፡፡
Next articleከ29 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጪ የተገነባው የጥርሀሆ ድልድይ ለአገልግሎት ዝግጁ ኹኗል።