ኢንደስትሪ ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ ለሳፋሪ አገልግሎት የሚውሉ መኪናዎችን በናሙናነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስረከበ።

35

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ቱሪዝም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች አንዱ እንደመሆኑ መሰረተ ልማትን እና አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ብሎም በዘርፉ ልምድን ማዳበር ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫ ነው። ብዛት ያላቸው ብሔራዊ ፓርኮች እና የዱር እንስሳት ሃብት ባላት ሀገራችን የሳፋሪ ልምምድን ማስፋፋት ቱሪስቶችን ለመሳብ ወሳኝ ተግባር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በየካቲት 2016 የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ100 ቀናት ግምገማ ወቅት ለቱሪዝም አገልግሎት የሚሰጡ የሳፋሪ ተሽከርካሪዎች እንዲመረቱ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሰጡትን አቅጣጫ ተከትሎ ኢንደስትሪ ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ ለሳፋሪ አገልግሎት ተሽከርካሪነት የተቀየሩ ባለአንድ ጋቢና ፒክ አፕ መኪናዎችን በናሙናነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስረክቧል።

መኪናዎቹን ለሳፋሪ አገልግሎት እንዲመቹ አድርጎ በመለወጥ ሂደት ውስጥ አምራቾች በሀገር ውስጥ በስፋት የመለወጥ ልምድ እና አቅም ለማዳበር ችለዋል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት በምርት ስራው የተሳተፉና አቅም ያላቸው አምራቾች የምርት ሥራውን ሂደት እንዲያስፋፉ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። መረጃው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሥራዎች ውጪ የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት አንችልም” ይሽሩ ዓለማየሁ (ዶ.ር.)
Next articleአቢሲኒያ ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀውን አሚን አዋርድ የሥራ ፈጠራ ውድድር ይፋ አደረገ፡፡