“ከሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሥራዎች ውጪ የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት አንችልም” ይሽሩ ዓለማየሁ (ዶ.ር.)

18

ደብረ ብርሃን: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)አራተኛው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሥራ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው። ኮንፈረንሱ “ለዘላቂ ልማት የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሥራዎች” በሚል መሪ ሃሳብ በዩኒቨርስቲው እና በዙሪያው የተሠሩ የፈጠራ ተግባራትን ለማበረታታት ታስቦ የተካሄደ ነው ተብሏል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የጥናት፣ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት አዝመራው አየሁ (ዶ.ር.) ዓለም የሚያውቀን ባለን የተፈጥሮ ፀጋ ሳይኾን ያንን ባለመጠቀማችን ነው ብለዋል። ያለንን ሃብት ለመጠቀም ደግሞ በቴክኖሎጂ እና ፈጠራው ዘርፍ ሀገር በቀል ዕውቀት እና የፈጠራ ባለሙያዎችን ማፍራት ይገባል ነው ያሉት።

በኮንፈረንሱ የተገኙት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩ ዓለማየሁ (ዶ.ር.) ከሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሥራዎች ውጪ የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት አንችልም ለዚህ ደግሞ በዘርፉ ዙሪያ ከታች ጀምሮ መሠራት አለበት ብለዋል። ሚኒስትሩ አክለውም ዘርፉን ለማበረታት መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሥራ ኮንፈረንስ በዘርፉ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች እንዲኹም የተማሪዎች እና የመምህራን የፈጠራ ሥራዎች የሚቀርቡ ሲኾን ለፈጠራ ሥራዎችም ዕውቅና እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።

ዘጋቢ፦ በላይ ተስፋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር ተወያዩ።
Next articleኢንደስትሪ ሚኒስቴር በሀገር ውስጥ ለሳፋሪ አገልግሎት የሚውሉ መኪናዎችን በናሙናነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስረከበ።