“የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ወግ እና ባሕላችን አጠናክረን መቀጠል አለብን” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

36

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ክልላዊ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በባሕር ዳር ከተማ አስጀምረዋል። ከርእሰ መሥተዳድሩ በተጨማሪ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ፣ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እና ሌሎች የክልሉ እንዲሁም የከተማዋ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በጎነት የታላቅነት መገለጫ ነው፤ መረዳዳት ደግሞ ባሕላችን እና ያደግንበት ነው ብለዋል። የበጎ አድራጎት ሥራዎች መንግሥታዊ ሥራዎች ኾነው እንዲከናወኑ እየተተገበሩ መኾናቸውን ተናግረዋል። በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በየዓመቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደሚሠራም ገልጸዋል። ትውልዱ በጎ ነገር ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በከተማዋ 300 ቤቶችን የመጠገን እና ማደስ፣ 100 ቤቶች ደግሞ እንደ አዲስ ተሠርተው ለአቅመ ደካሞች ይሠጣሉ ነው ያሉት። በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የመማር ማስተማር፣ የአረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ይሠራሉ ነው የተባሉት። ለከተማዋ የጎርፍ መጥለቅለቅ ችግር የኾኑ አካባቢዎችም እንደሚሠሩ ነው የተናገሩት። ከተማ አሥተዳደሩ ለሚሠራው ሥራ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው ሰላም እየተረጋገጠ መደበኛ ሥራ እየተሠራ መኾኑ ማሳያ ነው ብለዋል። ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ እንደ ክልል መጀመሩን ገልጸዋል። በጎ አድራጎት በታሪካችን፣ በማኅበረሰባችን አኗኗር፣ ባሕል የሚታወቅ እና ሲተገበር የነበረ ነው ብለዋል።

አቅም ያለው ለተቸገረ መደገፍ ያለ፣ የነበረ ወደፊትም እንዲጎለብት የሚፈለግ በጎ ባሕል እና ምግባር መኾኑን አስታውቀዋል። የመደጋገፍ እና የመረዳዳት ባሕል በሃይማኖት ተቋማትም የተለመደ እና ያለ መኾኑን ነው የተናገሩት። የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ወግ እና ባሕል የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል።

ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ሁል ጊዜ በውጭ እርዳታ መኖር የለባቸውም “በእኛ አቅም መደገፍ አለብን” ነው ያሉት። የእኛ የነበሩ ባሕሎችን ሌሎች ሀገራት ሕግ እና ሥርዓት አበጅተው ተቋም አደራጅተውላቸው በዓለም የታወቁ ሰውን የሚረዱ መኾናቸውን ነው ያነሱት።
ተቋማቱ የሀገራቸውን ገጽታ እንደሚገነቡ እና የሕዝባቸውን ክብር ከፍ እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት።

ቀደም ሲል የነበሩ ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ የበጎ አድራጎት አደረጃጀቶችን የበለጠ አጠናክረን ወደ ሥራ መግባት ይኖርብናል ብለዋል። የበጎ አድራጎት ሥራ በመንግሥት ብቻ የሚከወን አለመኾኑንም ገልጸዋል። ቀደም ሲል የነበረው እና በሂደት የተዳከመው በጎ አድራጎት ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል።

የመንግሥት ፖሊሲ ደሀ ተኮር መኾኑን ያነሱት ርእሰ መሥተዳድሩ የኑሮ ውድነትን በመከላከል፣ የቤት አቅርቦትን በማሻሻል፣ ሌሎች የፍጆታ እቃዎችን በድጎማ የማቅረብ ሥራ በመንግሥት እንደሚሠራ አንስተዋል። የበጎ ፋቃድ አገልግሎት ሥራ በማኅበረሰቡም ልማድ እና ወግ ኾኖ እንዲሠራ ይጠበቃል ነው ያሉት።

ዛሬ የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሌሎች በክልሉ ከተሞችም መካሄድ እንደሚገባው አሳስበዋል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በትምህርት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በጽዳት ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገን እና በመሥራት እንዲተገበር ይፈለጋል ነው ያሉት። ባለሃብቶች በገንዘባቸው፣ ባለሙያዎች በዕውቀታቸው፣ ወጣቶች በጉልበታቸው ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በመጪው የክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል። ከትምህርት ማጠናከሪያ፣ የቤቶች ልማት እና ከሌሎች ተግባራት ባለፈ የወባ ወረርሽኝ እና ሌሎች ተላላፊ የኾኑ በሽታዎችን መከላከል ይገባል ነው ያሉት። ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleእንቦጭን ለታዳሽ ሀይል እና ለግብርና ልማት ለማዋል የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሃሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር ተወያዩ።