
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ በርካታ ሥራዎች ሢሠራ ቆይቷል፡፡ አረሙን ለማስወገድ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል የተለያዩ ቴክኖሎጅዎችን በመጠቀም፣ ምርምሮችን በማካሄድ እንዲሁም የሰው ሀይል በማስተባበር የሰው ጉልበት መጠቀም ይገኙበታል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ካከናወኑት ምርምር መካከል የእንቦጭ አረምን ለባዮ ጋዝ፣ ለባዮ ቻር እና ለኮምፖስት ጥቅም ላይ በማዋል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ይገኝበታል፡፡
በቤተ ሙከራ ውስጥ ምርምር ሲደረግበት የቆየው ይህ ምርምር ውጤታማ በመኾኑ ወደ አርሶ አደሩ ለማድረስ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ህክም እና ሳይንስ ኮሌጅ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡ በፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ ዶክተር ካሳሁን ተገኝ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጅ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር ውለታው መኩሪያው፣ ዲኖች እና ዳይሬክተሮች እንዲሁም ከግብርና ቢሮ፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ መሪዎች፣ ባለሙያዎች እና ከአጋር ድርጅቶች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ዶክተር ውለታው መኩሪያው ናቡ ኢትዮጵያ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ከከተማው ጋር በርካታ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸው አሁንም ለዚህ ፕሮጀክት እውን መኾን ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ በፕሮጀክቱ 20 የሚኾኑ አርሶ አደሮች የእንቦጭ አረምን ለባዮ ጋዝ፣ ለባዮ ቻር እና ለኮምፖስት ጥቅም በማዋል በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ እንደሚኾኑ በመርሐ ግብሩ ተጠቅሷል፡፡
በፕሮጀክቱ አተገባበር እና ምንነት ዙሪያ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ እና ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ መምህር እንዲሁም ተመራማሪ ዶክተር ደሴ ጥበቡ ስለፕሮጀክቱ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ፕሮጀክቱን ውጤታማ ለማድረግ መከናወን ስለሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተሳታፊዎች ውይይት አድርገዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው ተሳታፊዎች በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግቢ በሚገኘው የሽንታ ምርምር ማዕከል በመገኘት በፕሮጀክቱ የተሠሩ የምርምር ውጤቶች (ባዮ ጋዝ፣ ባዮ ቻር እና ኮምፖስት) እንዲሁም የምርምር ሂደቱን በተመለከተ የጉብኝት መርሐ ግብር አካሂደዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!