
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ እንደገለጹት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለሚያቀርቡት መሰረተ ልማት የአገልግሎት ወጪን ሸፍኖ ተመጣጣኝ ትርፍ ለማግኘት ይሠራሉ። መንግሥት ደግሞ ለሕዝቡ ኤሌክትሪክ ተደራሽ የማድረግ አላማን ፍትሐዊ በኾነ አግባብ እንዲፈጸም የማድረግ ኀላፊነት አለበት ብለዋል።
በተቀመጠው የሕግ አግባብ የሁሉንም አካላት ፍላጎት አስጠብቆ ለማስቀጠል አዳጋች የኾኑ የዘርፉ እድገት ማነቆዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ከእነዚኽ መካከል አንዱ መንግሥት ኅብረተሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ላለማድረግ ሲል በሕግ የተቀመጠውን የታሪፍ ማሻሻያ ጊዜ ጠብቆ እንዲከለስ አለማድረጉን ጠቁመዋል።
ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም በየዓመቱ ተግባራዊ የተደረገው የኤሌክትሪክ ታሪፍ በ2014 ዓ.ም የተጠናቀቀ ሲኾን ላለፉት ሁለት ዓመታት ያለምንም ማሻሻያ መቆየቱን አንስተዋል። ይኽ ሁኔታ ተቋማቱ ጥራት ያለው እና አስተማማኝ አገልግሎት እንዳያቀርቡ ፣ አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት የፋይናንስ እጥረት እንዲገጥማቸው እና ከፍተኛ የእዳ ጫና ውስጥ እንዲዘፈቁ ምክንያት ኾኗል ብለዋል።
ኤፍቢሲ እንደዘገበው በተጨማሪም የኀይል አቅርቦት አማራጮችን ለማስፋት እና በኤሌክትሪክ ኤክስፖርት ዘርፉን ለመደገፍ አሁን ባለው ታሪፍ ማሰብ ፈታኝ እንደኾነም አንስተዋል። በዚኽም የኀይል አቅራቢ ተቋማቱ የታሪፍ ጥናት አዘጋጅተው ለባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ባቀረቡት መሰረት ታሪፍ ቅድመ ግምገማ በማከናወን ከኅብረተሰቡ በተለያዩ መንገዶች አስተያየት እንቀበላለን ነው ያሉት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!