
ሰቆጣ: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ማኅበረ ቅዱሳን በአበርገሌ ወረዳ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ170 ኩንታል በላይ የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ ድጋፍ አደረገ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የማኅበረ ቅዱሳን ከተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶች እና ማኅበራት ያሠባሠበውን ከ178 ኩንታል በላይ የዕለት ደራሽ ሰብዓዊ ድጋፍ በአበርገሌ ወረዳ ለሚገኙ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል እማሆይ አበቡ ባለፋት ወራት የድጋፍ እጥረት በመኖሩ ሕጻናት፣ አጥቢ እናቶች እና አዛውንቶች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መቆየታቸውን ተናግረዋል። አቶ ወለ ብሬ በበኩላቸው የድጋፍ እጥረት በመኖሩ ምክንያት ቤተሠቦቻቸው የከፋ ችግር ውስጥ እንደቆዩ ጠቅሰው ስለተደረገላቸው ድጋፍ ምሥጋና አቅርበዋል።
ማኅበረ ቅዱሳን ከአሁን በፊትም በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች አጋርነቱን አሳይቷል ያሉት በአዲስ አበባ የማኅበሩ ተወካይ አግአዚ አብርሃ ናቸው። ድጋፋንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል። በአዲስ አበባ ግሎባል አሊያንስ ድርጅት ተወካይ በፍቃዱ ዓባይ በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ አሳሳቢ መኾኑን ጠቅሰው ሌሎች ድርጅቶችም የሰብዓዊ እና የእንሰሳት መኖ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በአበርገሌ ወረዳ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከ67 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ሲኾን በአንደኛ ዙር ከ49 ሺህ በላይ ሰዎች መደገፋቸውን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ መሠረት ወልደየስ ተናግረዋል። ማኅበሩ ያደረገው 178 ኩንታል ድጋፍ ለ113 የማኅበረሰብ ክፍሎች የወር ቀለብ እንደሚኾን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የማኅበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ በሰብል ልማት ማተኮር እንደሚገባ ምክትል ኀላፊዋ አሳስበዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል ከ155 ሺህ ኩንታል በላይ የሚገመት ድጋፍ 229 ሺህ በላይ ማኅበረሰቦች ባለፋት ወራት ድጋፍ መደረጉን የአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምህረት መላኩ ገልጸዋል።
ከሚደረጉ ሰብዓዊ ድጋፎች ባሻገር በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባለፋት ሰባት ወራት ብቻ ከ14 ሺህ 397 በላይ እንሰሳት መሞታቸውን ጠቅሰዋል። በድርቁ ለተጎዱ ወገኖች አጋርነታቸውን ላሳዩ ድርጅቶች፣ ማኅበራት እና ግለሰቦች ምሥጋና ያቀረቡት አቶ ምህረት በቀጣይም የእንሰሳት መኖ ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!