
ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሰው ሠራሽ አስተውሎት የኮምፒውተር ፕሮግራሞች በራሳቸው እንዲያስቡ እና እንደማሩ ማድረግ የሚያስችል ትኩስ የቴክኖሎጂ በረከት ነው። የሰው ልጅ ያለውን ዓይነት አስተውሎት ማሽኖች እንዲላበሱ እና በሰው ልጆች ብቻ ይሠሩ የነበሩ ተግባራትን እንደከውኑ የሚያስችል ነው።
ማሽኖች እንዲረዱ፣ በአመክንዮ እንዲሠሩ፣ እንዲማሩ እና ልክ እንደ ሰዎች ተግባቦት እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል። ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሚኖረው የመፈጸም አቅም በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይመደባል። የመጀመሪያው ነጠላ ተግባር ላይ የሚያተኩር እና ከአንድ ዓይነት ተግባር ውጭ ማከናወን የማይችል የሰው ሠራሽ አስተውሎት ነው።
ሁለተኛው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዓይነት ደግሞ የሰው ልጅ ለመሥራት የሚችለውን ተግባር መከወን የሚችል ነው። በዚህኛው መደብ የምናገኘው የሰው ሠራሽ አስተውሎት መረዳት እና በራሱ መማር ይችላል። ሦስተኛው እስከ አሁን በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ያለ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሲኾን የሰው ልጅ መሥራት ከሚችለው በላይ ውስብስብ ተግባራትን ማከናውን የሚችል ነው። ለወደፊት ተግባራዊ ይኾናል ተብሎ የሚታሰብ ነው።
ሰው ሠራሽ አስተውሎት በርካታ የሰውን ልጅ የሕይዎት ውጣ ውረድ ማቅለል የቻሉ ጥቅሞች አሉት። ጉልበትን፣ ጊዜን እና ገንዘብን በመቆጠብ ጉልህ አስተዋጽዖን እያበረከተ እና ምርታማነትን ከጥራት ጋር እየጨመረ ያለ ዘመን ወለድ በረከት ነው። እጅግ ብዙ ጥቅሞች ያሉት ሲኾን በተለያዩ ሁኔታዎች የሰው ልጅ በሥራ ላይ የሚፈጥራቸውን ስህተቶች የማይፈጽም መኾኑ አስደናቂ ያደርገዋል። እጅግ ብዙ እና ውስብስብ ተግባራትን በትክክል እና በጥራት መሥራት ይችላል። እያንዳንዷን ተግባር የሚያከናውነው ቀድመው የተሰጡትን መረጃዎች መሠረት በማድረግ እና ሥራዎችን ለመከወን ሥልተ ቀመሮች የሚጠቀም በመኾኑ ጥራትን እንዲያስጠበቅ ይረዳዋል።
የሰው ልጅ ለማድረግ ቢሞክር አስቸጋሪ እና ለሕይዎት ሥጋት የሚኾኑበትን ተግባራት ለማከናውን ይህን አስተውሎት የተላበሱ ሮቦቶች ማከናውን ይችላሉ። ጠፈር ሄደው የምርምር ተግባራትን ማከናውን፣ ውቂያኖስ ጠልቀው መረጃ መሠብሠብ፣ የተጠመዱ ፈንጂዎች መክሸፋቸውን እና አለመክሸፋቸውን ማረጋገጥ እና ሌሎች ለሰው ልጅ ምቹ ያልኾኑ ሁኔታዎች ላይ ጠቃሚ ሥራን ይሠራሉ።
በተጨማሪም በመረጃዎች ላይ ተመሥርተው ውሳኔ መስጠት፣ የሕክምና ምርመራ ላይ ድጋፍ ማድረግ፣ ተሽከርካሪዎች ራሳቸውን ችለው ያለ ሾፌር እንዲንቀሳቀሱ ለማደረግ ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። በጎ ጎኖቹን እንዳየነው ሁሉ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ውስንነቶችም አሉት። የመጀመሪያው የሰውን ልጅ አስተውሎት የተላበሱ ማሽኖችን መሥራት እና ወደ ተግባር ለማስገባት ያለው ወጭ ቀላል የሚባል ባለመኾኑ ለመተግበር አስቸጋሪ ያደርገዋል።
የሚሰጠውን መረጃ ብቻ መሠረት አድርጎ የሚሠራ በመኾኑ ፈጠራ እና አዲስ ነገር መጨመር አይችልም። የሰውን የሥራ ዕድል ሊሻማ ይችላል እና ሰው እንዲሰንፍ ያደርጋል የሚሉ ሥጋቶችም አሉበት። ለበጎ ተግባር ተብሎ የተዘጋጀው የሰው ሠራሽ አስተዋሎት ለመጥፎ ዓላማም ስለሚውል የሥነ ምግባር እና የሞራል ጉዳዮች ላይ ክፍተቶችም አሉበት።
ከብዙ በጥቂቱ በጎ ጎኑን እና ውስንነቱን ለማየት ሞከርን እንጂ የሰው ሠራሽ አስተውሎት እጅግ በጣም ብዙ መልካም ነገሮችን መሥራት የሚያስችል አቅም ያለው እና ከአጠቃቀም ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮችም አብረው የሚነሱበት አዲስ የቴክኖሎጂ እፍታ ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!