በሚቀጥሉት ቀናት የሚጠበቀው ዕርጥበት የመኸር ሰብሎችን ለመዝራት እና ማሳን ለማዘጋጀት እንደሚያግዝ ተገለጸ፡፡

14

ባሕር ዳር: ሰኔ 06/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሚቀጥሉት ቀናት የሚጠበቀው እርጥበት አስቀድመው የሚዘሩ የመኸር ሰብሎችን ለመዝራት እና ማሳን ለማዘጋጀት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ በሚቀጥሉት ዘጠኝ ቀናት የሚጠበቀው እርጥበት አስቀድመው የሚዘሩ የመኸር ሰብሎችን በወቅቱ ለመዝራት እና ማሳን ለማዘጋጀት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው አስታውቋል።

በልግ አብቃይ በኾኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ዘግይተው ለተዘሩ እና ፍሬ በመሙላት ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎች፣ ለቋሚ አትክልቶች እና ፍራፍሬዎች የውኃ ፍላጎትን ከማሟላት አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተመላክቷል። በምዕራብ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚጠበቀው የእርጥበት ሁኔታ የረጅም ጊዜ ሰብሎችን ለመዝራት፣ ለቋሚ ተክሎች፣ በአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ለተተከሉ እና ለሚተከሉ ችግኞች እድገት ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።

በሌላ በኩል በሚቀጥሉት ቀናት በዓባይ፣ በላይኛው እና በመካከለኛው ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ አዋሽ፣ ተከዜና በጥቂት የአፋር ደናክል ተፋሰሶች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት ያገኛሉ። በተፋሰሶች ላይ የሚኖረውን የገፀ ምድርም ኾነ የከርሰ ምድር የውኃ ሃብትን ያሻሽላል፤ ለመስኖም ኾነ ለኃይል ማመንጫነት የሚያገለግሉ ግድቦች የውኃ መጠን ያሻሽላል ተብሏል፡፡

ኢዜአ እንደዘገበው በሚቀጥሉት ዘጠኝ ቀናት ለክረምት መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ከቀን ወደ ቀን እየተስፋፉ እና እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ ተመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የገበያ ትሥሥር እጥረት ለኪሳራ እየዳረገን ነው” በወልቃይት ጠገዴ ሽንኩርት አምራች ባለሃብት
Next articleርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን አስጀመሩ።