ከ250 ሚሊየን ዶላር በላይ በኾነ ወጭ 2 ሺህ የጤና ማዕከላትን መገንባት የሚያስችል ሥምምነት ተፈረመ።

73

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች 2 ሺህ የጤና ማዕከላትን ለመገንባት የጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች ሦስት ተቋማት የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረሙ።

ሥምምነቱን የጤና ሚኒስቴር፣ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እና የሩስያ ፓን-አፍሪካ ፐብሊክ ፕራይቬት አጋርነት ለልማት የተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ተወካዮች ፈርመውታል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በሥምምነቱ መሠረት ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመታት እንደሚቆይና 2 ሺህ የጤና ማዕከላትን ለመገንባት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ማዕከላቱ በዋናነት በእናቶች እና ሕጻናት ጤና፣ በአረጋውያን፣ በወጣቶች እንዲሁም በወሊድ፣ በክትባት፣ በቤተሰበ እቅድ እና በሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ተጠቁሟል።

ይኽም ለማኅበረሰቡ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ነው ያሉት።

የሚገነቡት የጤና ማዕከላት እያንዳንዳቸው ከ2 ሺህ እስከ 5 ሺህ የሚጠጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የተለያዩ የሕክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላል ማለታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመላክታል።

ማዕከላቱን ለመገንባት ከ250 ሚሊየን ዶላር በላይ እንደሚወጣ እና ወጪውም በሩስያ ፓን-አፍሪካ ፐብሊክ ፕራይቬት አጋርነት ለልማት የሚሸፈን መኾኑን ጠቁመዋል።

የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው ሥምምነቱ የእናቶችን ብሎም የህፃናትን ጤና ለመጠበቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
በመኾኑም ሚኒስቴሩ ለፕሮጀክቱ እውን መኾን የሚጠበቅበትን ሚና ይጫወታል ነው ያሉት።

የሩስያ የፓን-አፍሪካ ፐብሊክ ፕራይቬት አጋርነት ለልማት ግብረ-ሰናይ ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኦክሳና ማዮሮቫ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የዜጎችን ጤናማ ሕይዎት ለማስጠበቅ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ይህን ፕሮጀክት ወደ ሀገሪቱ እንዲመጣ ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ እውን መኾኑን የገለጹት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ (ዶ.ር) ናቸው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

 

Previous articleለሕጻናት ጤና እጅግ ጠንቅ የኾነ የዱቄት ወተት በገበያ ላይ ሲሸጥ ተያዘ፡፡
Next article“የገበያ ትሥሥር እጥረት ለኪሳራ እየዳረገን ነው” በወልቃይት ጠገዴ ሽንኩርት አምራች ባለሃብት