
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ባሕር ዳር ቅርንጫፍ እና የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ለሕጻናት ጤና ጠንቅ የኾኑ የዱቄት የወተት ዓይነቶች ገበያ መዋላቸውን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በደብዳቤ እንዳሳዎቃቸው ተናግረዋል። ምርቱም በአምስት ቀናት ውስጥ እንዲሠበሠብም ታዝዟል።
በኢትዮጵያ ምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን የባሕር ዳር ቅርንጫፍ የምግብ ኢንስፔክሽን ባለሙያ መለሠ እንግዳየሁ እንዳሉት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባሳወቀው መሠረት ባደረጉት አሰሳ “ኑራ ሱፐር ኢንስታንት የዱቄት ወተት” የተባለ ለጤና ጠንቅ የኾነ ወተት ገበያ ላይ ሲሸጥ ይዘዋል።
“ኑራ ሱፐር ኢንስታንት የዱቄት ወተት” በተባለው ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው የአርሰኒክ እና ዚንክ ኬሚካሎች ተገኝቶበታል ነው ያሉት።
እነዚህ ኬሚካሎች ለምግብነት በሳይንስ ከሚፈቀደው መጠን በላይ ሲኾኑ ደግሞ ለሕጻናት ጤና እጅግ ጠንቅ ናቸው ብለዋል።
ባለሙያው በ”ኑራ ሱፐር ኢንስታንት የዱቄት ወተት” ውስጥ የፕሮቲን እና የፋት መጠኑ ደግሞ ሳይንሱ ከሚያዘው መጠን በጣም ያነሰ ኾኖ ተገኝቷል ነው ያሉት። ስለኾነም ገበያ ላይ በተደረገ ቅንጅታዊ አሰሳ ምርቱ እየተሠበሠበ ነው ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ ለሕጻናት ጤና ጠንቅ የኾነ “ሱልጣን ኢንስታንት ፉል ክሪም የዱቄት ወተት” ገበያ ላይ በመዋሉ ተከታትሎ ለመያዝ እየታሰሰ በመኾኑ የኅብረተሰቡን የነቃ ተሳትፎ ጠይቀዋል።
ኅብረተሰቡ የሚገዛውን የሀገር ውስጥም ይሁን ከውጭ ሀገር የገባን የታሸገ ምግብ በጥንቃቄ ፈትሾ መግዛት እንዳለበት አሳስበዋል።
በአማራ ክልል የንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ሪጉሌሽን እና ኢንስፔክሽን ባለሙያ አበበ አዲሱ ለሕጻናት ጤና ጠንቅ የኾነው “ኑራ ሱፐር ኢንስታንት የዱቄት ወተት” ገበያ ላይ አየተሠበሠበ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
“ሱልጣን ኢንስታንት ፉል ክሪም የዱቄት ወተት ” በየሱፐር ማርኬቱ እየታሰሰ ነው ብለዋል። የሁሉንም ቅንጅታዊ እገዛም ጠይቀዋል።
አቶ አበበ በክልሉ ለሁሉም ዞን እና ብሔረሰብ አሥተዳደሮች በተዋረድ እነዚህን ለሕጻናት ጤና ጎጅ የኾኑ የወተት ዱቄቶችን ገበያ ላይ አስሰው እንዲይዙ በደብዳቤ እንደተገለጸላቸው ተናግረዋል።
ባለሙያው ጨምረው እንደተናገሩት በተወሰኑ አካላት ብቻ ሕገ ወጥ ተግባርን መቆጣጠር ስለማይቻል ኅብረተሰቡም እነዚህን ለጤና ጠንቅ የኾኑ የሕጻናት የዱቄት የወተት ዓይነቶችን አስሶ በማግኘት ሊደርስ የሚችልን ሰብዓዊ ጉዳት አስቀድሞ እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!