የካላዛር በሸታን ለማጥፋት የሚስችል ስትራቴጅክ ዕቅድ ይፋ ኾነ።

37

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የካላዛር በሸታን ለማጥፋት የሚስችል ስትራቴጅክ ዕቅድ ይፋ ኾኗል። ከሰኔ 3 እስከ 5/2016 ዓ.ም ድረስ የጤና ሚኒስቴር ከዓለም ጤና ድርጅት እና አጋሮቹ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ እየተደረገ ባለው የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የካላዛር በሽታ የማጥፋት ፕሮግራም ኀላፊዎች የውይይት መድረክ ላይ ነው የስትራቴጂክ ዕቅዱ ይፋ የተደረገው።

በውይይቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ዱጉማ (ዶ.ር) በዓለም አቀፍ ደረጃ የካላዛር በሽታ ስርጭት 70 በመቶ ድርሻ የሚይዘው ከምሥራቅ አፍሪካ መኾኑን እና በኢትዮጵያ ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የሚኾን የማኅበረሰብ ክፍል ካላዛር እንዲሁም ወደ 30 ሚሊዮን የሚኾነው የማኅበረሰብ ክፍል ለቆዳ ላይ ሊሺማኒያሲስ ተጋላጭ እንደኾነ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀደም ብሎ የተሠራውን የበሽታ ስርጭት ጥናትን ጠቅሰው ገልጸዋል፡፡

ትኩረት የሚሹ የሀሩራማ በሸታዎች የስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ የካላዛር ወይም ሊሽማኒያሲስ በሸታ መከላከል፥ መቆጣጠር እና ጥራቱን የጠበቀ ህክምና ለመስጠት የሚያስችሉ ዕቅዶችን በማካተት በርካታ ሥራዎች መሠራቱን አብራርተዋል፡፡ ዶክተር ደረጀ ጤና ሚኒስቴር የሦስተኛ የሀሩራማ በሸታዎች ስትራቴጂክ ዕቅድን በመተግበር በሸታው የኅብረተሰብ ጤና ችግር ወደ ማይኾንበት ደረጃ ለማውረድ የተጠናከረ ሥራ እየተሠራ እንደኾነ አስረድተዋል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው አሕጉራዊ የካላዛር በሽታን የማስወገድ ስትራቴጂ በተለይም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ውስጥ የበሽታ ጫና እና የሞት አደጋ በመቀነስ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል። ዶክተር ደረጀ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ የካላዛር በሽታን ለማጥፋት ሀገራቶቹ እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ያሳዩትን ቁርጠኝነት ያደነቁ ሲኾን መድረኩ መዘጋጀቱ እና መሪ ዕቅዱ መጽደቁ በሽታውን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

በጤና ሚስቴር የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ሥራ አሥፈሚ ዶክተር ሕይዎት ሰለሞን እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር በ2030 የካላዛር በሽታ ስርጭት የማኅበረሰብ የጤና ችግር በማይኾንበት ደረጃ ለመቀነስ ኢትዮጵያ ከመቼውም በላይ ቁርጠኛ መኾኗን ተናግረዋል፡፡ ዶክተር ሕይወት የበሸታውን ጫና ለመቀነስ የተሠሩ ዐበይት ሥራዎችን ያነሱ ሲኾን የህክምናው ተደራሽነትን ከማረጋገጥ አንጻር ስርጭቱ ባለባቸው አካባቢዎች 56 የምርመራ እና 31 የቪሲሪያል ሊሺሚኒያሲስ የህክምና ማዕከላትን በማቋቋም አገልግሎቱን ማቅረብ መቻሉን ነው የገለጹት፡፡

በዚህም በህመሙ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ2022 ከነበረው 3 ነጥብ 9 በመቶ በ2024 ወደ 0 ነጥብ 8 በመቶ መቀነስ መቻሉን አስታውቀዋል። የመንግሥትን ሙሉ አቅም በመጠቀም እና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እንደ ሀገር የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት እንደሚሠራ ዶክተር ሕይዎት ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ከዓለም አቀፍ እና ከሀገር ውስጥ ካሉ ሳይንሳዊ እና የቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴዎች እንዲሁም ከትምህርት እና የምርምር ተቋማት ጋር በቅርበት የሚሠሩ ተግባራትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። የዘጠኙ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ተወካዮች በመድረኩ በሀገሮቻቸው ውስጥ የካላዛር በሽታ ስርጭት ምን እንደሚመስል እና ስለበሽታው አጠቃላይ ሁኔታ፣ በሽታውን ለማጥፋት እየተደረገ ያለው ጥረት እና በመንግሥታቱ በኩል ያለውን ቁርጠኝነት አስቀምጠዋል።

የጤና ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳለው የዓለም ጤና ድርጀት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአፍሪካ ሲዲሲ፥ የዘጠኙ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ተወካዮች፣ የድራግ ፎር ነግሌክትድ ዲዚዝ ኢኒሸቲቭን ጨምሮ የካላዛር (ሊሽማኒያሲስ) በሸታ ላይ በቅርበት የሚሠሩ አጋር ድርጅቶች እንዲሁም የተለያዩ የምርምር ተቋማት ተወካዮች በመድረኩ ተገኝተዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ተጋግዞ ችግርን በመፍታት ከግጭት አስተሳሰብ መውጣት ያስፈልጋል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር )
Next articleለሕጻናት ጤና እጅግ ጠንቅ የኾነ የዱቄት ወተት በገበያ ላይ ሲሸጥ ተያዘ፡፡