“ተጋግዞ ችግርን በመፍታት ከግጭት አስተሳሰብ መውጣት ያስፈልጋል” ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር )

18

ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በደብረ ማርቆስ ከተማ ለአቅመ ደካማ የማኅበረሰብ ክፍሎች መጠለያ ለመገንባት በተዘጋጀ ቦታ የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ እና አቅመ ደካማ ለኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ቤት የማደስ በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር ተከናውኗል።

ኑሯቸውን በደብረ ማርቆስ ከተማ ያደረጉት ወይዘሮ ሙሉጎጃም ወተሬ ባለባቸው የአቅም እጥረት እና የጤና ችግር ምክንያት የዘመመ እና ጣራው የሚያፈስ አነስተኛ ጎጇቸውን በራሳቸው አቅም ለመጠገን አቅም በማጣታቸው በችግር ውስጥ ኾነው በርካታ ዓመታትን ከብርድ እና ዝናብ ጋር አሳልፈዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ችግራቸውን ለመፍታት በማሰብ አሮጌ ቤታቸውን ሙሉ ለሙሉ በአዲስ ለመሥራት በመኖሪያ ቦታቸው በመገኘቱ ለተደረገላቸው በጎ ተግባር ምሥጋና አቅርበዋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ተግባሩ የክረምት በጎፈቃድ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካል መኾኑን ገልጸዋል፡፡

“በኅብረተሰብ አቅም የኅብረተሰብ ችግርን በመፍታት፤ እርስ በእርስ በመደጋገፍ ከግጭት አስተሳሰብ መውጣት ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡ በከተማ አሥተዳደሩ የንጉስ ተክለሃይማኖት ክፍለ ከተማ ሥራ አሥፈፃሚ አየለ አድማሱ ግንባታው ሲጠናቀቅ 14 የሚደርሱ አቅመ ደካማ እማወራዎችን እና አባወራዎችን የመጠለያ ችግር እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡

ግንባታው ከመጠለያነት ባለፈ የቤቱ ተጠቃሚዎች ኢኮኖሚያቸውን ሊያሳድጉበት የሚችሉ አሠራሮች በግንባታው መካተታቸውን አንስተዋል፡፡ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ መንበሩ ዘውዴ የመኖሪያ ቤት ግንባታውን በበጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች እና ተቋማት ተሳትፎ ገንብቶ በማጠናቀቅ በተያዘለት ጊዜ ለተጠቃሚዎች ለማስረከብ እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡

በከተማ አሥተዳደሩ በችግር ውስጥ ያሉ ነዋሪዎችን ችግር በቅርበት መፍታት እንዲቻል ሰላም ወሳኝ መኾኑን አንስተዋል። ከፌዴራል፣ ከክልል እና ከከተማ አሥተዳደሩ የተውጣጡ መሪዎች እና የሥራ ኀላፊዎች በደብረ ማርቆስ ከተማ በሥራ ላይ ያሉ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ያሉበትን ደረጃ ተዟዙረው ተመልክተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጎንደር ከተማ ሕዝብ በወቅታዊ የሰላም እና የጸጥታ፤ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዬች ላይ እየመከረ ነው፡፡
Next articleየካላዛር በሸታን ለማጥፋት የሚስችል ስትራቴጅክ ዕቅድ ይፋ ኾነ።