
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ከሰኔ4-5/2016ዓ.ም ድረስ ሲሰጥ የነበረው የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኅላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ.ር) ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽአ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ፈተናውን ከማጓጓዝ ጀምሮ ተማሪዎች ተፈትነው እስከሚያጠናቅቁ ድረስ ለተሳተፉ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ በየደረጃው የሚገኙ ትምህርት ዘርፉ መሪዎች፣ ወላጆች፣ የትምህርት ባለድርሻ አካላት እና ተማሪዎችን ለስኬታማነቱ ለነበራቸው አበርክቶ ኀላፊዋ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
በቀጣይ ከሰኔ 13-14/2016 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚሰጠው የ6ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና በሰላም እንዲጠናቀቅ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ሁሉ የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ቢሮ ኀላፊዋ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!