“የጸጥታ የችግሩ መፍቻ መንገድ ከሕዝብ ጋር በተገቢው መንገድ መመካከር መኾኑን ነው” ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር.)

15

ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በውቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል። የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች ባነሱት ሃሳብ ሁሉም ዜጋ ለሰላሙ መጠበቅ ኀላፊነት አለበት። በየመስሪያ ቤቱ ያሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ማኀበረሰቡን እያማረሩ እንደኾነ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ልዩነቶችን በሰከነ መንፈስ በመነጋገር እና በመወያያት መፍታት አለመቻል ክልሉን ለተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኀበራዊ ቀውሶች ዳርጓል ብለዋል። የውይይቱ ተሳታፊ የመንግሥት ሠራተኞች አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነት የመንግሥት ሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ እያወሳሰበ እንደኾነም አንስተዋል።

የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ለችግሮቹ የውይይት አማራጮችን ማስቀደም እንደ መፍትሄ ሃሳብ የቀረበ ሲኾን ለዚህም የበኩላችውን ሚና በመውጣት የተረጋጋ ክልል እና ሕዝብ እንዲኖር እንደሚሠሩ ተናግረዋል። የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙሀመድአሚን የሱፍ የመንግሥት ሠራተኛው ሕዝብ የሚማረርበትን የአገልግሎት አሰጣጥ ማስተካክል እንዳለበት አሳስበዋል። እንደ መንግሥትም አስፈላጊውን የማስተካከያ ሥራዎችን ለማከናወን ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናችውን ጠቅሰው በተለይም የመንግሥት ሠራተኛውን የቤት ባለቤት ለማድረግ ሥራዎች ተጀምረዋል ብለዋል ከንቲባ ሙሀመድአሚን። የአማራ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) በአሁኑ ወቅት በክልሉ በአብዛኛው አካባቢ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ገልጸዋል።

የተከሰተው ቀውስ ውጫዊ እና ውስጣዊ ምክንያቶች አሉት ያሉት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊው “የችግሩ መፍቻ መንገድ ከሕዝብ ጋር በተገቢው መንገድ መመካከር ነው” ብለዋል። የጦርነቱን አውድማ ክልሉ ላይ አድርገው እርስ በእርስ እንድንበላላ የሚያደርጉ ኃይሎችን ሕዝብ በተገቢው መንገድ በማጋለጥ የመፍትሄው አካል መኾን አለበት ብለዋል። በየምእራፉ በተሠሩት ሥራዎች ማኅበረሰቡ ችግሩን በተገቢው መንገድ እንዲረዱ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት ችግሩ ከተፈጠረ ጀምሮ ያለው አቋም ችግሩ ከጠመንጃ ውጭ እንዲፈታ ማድረግ መኾኑን በማንሳት ይህ ሃሳብ አሁንም እንደጸና ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀን አምባቸው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ትምህርት ላይ መሥራት ነገን መሥራት እና ሀገርን መሥራት ስለኾነ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ሊተባበር ይገባል” ከንቲባ ደሴ መኮንን
Next articleየኮንትራት ቅጥር ማስታወቂያ ! ጊዜያዊ የረዥም ጊዜ/ የኮንትራት ቅጥር ማስታወቂያ፦