
ባሕር ዳር: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከትናንት ጀምሮ ሲሰጥ የነበረው የ2016 ዓ.ም የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና በሰላም ተጠናቅቋል፡፡ በከተማ አሥተዳደር ደረጃ ከትናንት ጀምሮ ሲሰጥ የነበረው ክልላዊ የስምንተኛ ክፍል ፈተና በሁሉም የከተማዋ የመፈተኛ ጣቢያዎች በሰላም መጠናቀቁን የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ እየበሩ አእምሮ ገልጸዋል።
ትምህርት የነገ ትውልድ መሰረት መኾኑን የገለጹት ኃላፊው በሁሉም የመፈተኛ ቦታዎች ተማሪዎች ያለምንም ችግር በሰላም እንዲፈተኑ መደረጉና በሰላም መጠናቀቁ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል። የከተማውን መሪዎችና የጸጥታ አካላት፣ መላ ሕዝቡን እንዲሁም የትምህርት ተቋማትንም አመሥግነዋል።
ኃላፊው በከተማ አሥተዳደሩ በዘንድሮው 2016 ዓ.ም ክልላዊ የ8ኛ ክፍል ፈተና 1 ሺህ 649 ተማሪዎች በ18 የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች መፈተናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን በከተማ አሥተዳደሩ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲቋረጥና የነገ የሀገር ተረካቢዎችን ተስፋ ለማጨለም ብዙ ጥረት ቢደረግም እንደ ከተማ በትኩረት በመሥራታችን በከተማችን በሁሉም ትምህርት ቤቶች ክልላዊ የ8ኛ ክፍል ፈተናውን ማስፈተን ችለናል ብለዋል።
ትምህርት ላይ መሥራት ነገን መሥራት እና ሀገርን መሥራት ስለሆነ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ሊተባበርና በዘላቂነት ተባብሮ ሊሠራ ይገባልም ብለዋል ከንቲባው። በቀጣይ የ6ኛ እና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በተያዘው መርሐ ግብር መሰረት ለማስፈተን ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መኾኑን የገለጹት ከንቲባው ለቀጣይ ተግባራት ሁሉም ተጋግዞ መሥራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!