
ሁመራ: ሰኔ 05/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በሕወሀት ታጣቂዎች አማራ በመኾናቸው ብቻ በማይካድራ ከተማ 1 ሺህ 644 ንጹሐን አማራዎች በግፍ መጨፍጨፋቸው የሚታወስ ነው። ለነጻነታቸው እና ለአማራዊ ማንነታቸው በሕወሀት ታጣቂዎች የግፍ ጽዋን የተጎነጩት ሰማዕታት በወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ልብ ውስጥ ላይነጥፉ ለዘለዓለም ነግሰዋል።
የዞኑ አሥተዳደር “የጥቅምት 30 ሰማዕታትን መቼም አንረሳችሁም” በሚል መሪ መልዕክት በማይካድራ ከተማ የሰማዕታት መታሰቢያ ሀውልት ለመገንባት የሚያስችል የዲዛይን ትውውቅ መርሐ ግብር አካሂዷል። የመታሰቢያ ሀውልቱ በሙዚየምነት እንደሚሠራ የተገለጸ ሲኾን በ3 ሺህ 136 ካሬ መሬት ላይ እንደሚገነባም ነው የተነገረው።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው “የማይካድራ ከተማ ሰማዕታትን መቼም አንረሳቸውም” ጊዜው የሥራ እና የትግል በመኾኑ ሰማዕታት ለአማራነታቸው የከፈሉትን ሰማዕትነት ለማሰብ በስማቸው መታሰቢያ ሀውልት እንገነባለን ብለዋል። ጥቅምት 30 በማይካድራ ሰማዕታት ላይ የተፈጸመው የዘር ጭፍጨፋ የዘመን ግፈኞች የኾኑትን የሕወሀት ታጣቂዎች የሀገር ክህደት እና የክፋቱ ጥግ ማሳያ መኾኑን ተናግረዋል።
ይህ ሀውልት ሲጠናቀቅ የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ትግል “አማራ ነን እንጂ አማራ እንሁን አላልንም” የሚለው ጉልህ ምልክት ኾኖ እንደማሳያ የሚያገለግል ነው ያሉት አቶ አሸተ የማይካድራ ሰማዕታት በሰው ልጅ አዕምሮ እና ልብ ማህተም ኾኖ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል። ሙዚየሙ ሲገነባ የዳግማዊ አያናዝጊ ቤት-ሞሎ ቤተ መንግሥት እና ከታሪካዊ የጎንደር-የፋሲል አብያተ መንግሥታት ጋር በታሪክ ተጣጥሞ የሚሠራ ሀውልት መኾኑ ትልቅ የትግሉ ድል እና ስኬት እንደኾነም ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ የሙዚየሙ መገንባት የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ የከፈለውን መስዋዕትነት የሚያሳይ ነው ብለዋል። የሙዚየሙ መገንባት ጦርነት የሚያደርሰውን እልቂት የሚያሳይ ፍቅር እና አንድነትን ማስቀደም እንደሚገባ የሚያስተምር መኾኑን አንስተዋል።
በውስጡ ቤተ መጽሐፍትን፣ የሰማዕታትን ታሪክ እና ሌሎች የወልቃይትን ታሪክ፣ ባሕል እና ወግ የሚያሳዩ ነገሮችን አካቶ ይይዛል ነው ያሉት። በ100 ሚሊዮን ብር በጀት በሕዝብ ተሳትፎ እንደሚገነባ ያነሱት የማይካድራ ከተማ ከንቲባ ሙሉጌታ መብራቱ በሙዚየሙ ግንባታ ሕዝቡ ደስተኛ ነው ብለዋል።
ግንባታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ከኅብረተሰቡ ጋር በመኾን በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!